ምዕራፍ 47
1ዮሴፍም ገባ ለፈርዖንም ነገረው እንዲህ ብሎ። አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውም ላሞቻቸውም ያላቸውም ሁሉ ከከነዓን ምድር ወጡ፤ እነርሱም እነሆ በጌሤም ምድር ናቸው።
2ከወንድሞቹም አምስት ሰዎችን ወስዶ በፈርዖን ፊት አቆማቸው።
3ፈርዖንም ወንድሞቹን። ሥራችሁ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም ፈርዖንን። እኛ ባሪያዎችህ፥ እኛም አባቶቻችንም፥ በግ አርቢዎች ነን አሉት።
4ፈርዖንንም እንዲህ አሉት። በምድር ልንቀመጥ በእንግድነት መጣን፥ የባርያዎችህ በጎች የሚሰማሩበት ስፍራ የለምና፤ ራብ በከነዓን ምድር እጅግ ጸንቶአልና፤ አሁንም ባሪያዎችህ በጌሤም ምድር እንድንቀመጥ እንለምንሃለን።
5ፈርዖንም ዮሴፍን ተናገረው እንዲህ ብሎ። አባትህና ወንድሞችህ መጥተውልሃል፤
6የግብፅ ምድር በፊትህ ናት፤ በመልካሙ ምድር አባትህንና ወንድሞችህን አኑራቸው፤ በጌሤም ምድር ይኑሩ፤ ከእነርሱም ውስጥ እውቀት ያላቸውን ሰዎች ታውቅ እንደ ሆነ በእንስሶቼ ላይ አለቆች አድርጋቸው።
7ዮሴፍም ያዕቆብን አባቱን አስገብቶ በፈርዖን ፊት አቆመው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው።
8ፈርዖንም ያዕቆብን። የዕድሜህ ዘመን ስንት ዓመት ነው? አለው።
9ያዕቆብም ለፈርዖን አለው። የእንግድነቴ ዘመን መቶ ሠላሳ ዓመት ነው፤ የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ሆኑብኝ፥ አባቶቼ በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያህሉም።
10ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው ከፈርዖንም ፊት ወጣ።
11ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን አኖረ፥ ፈርዖን እንዳዘዘም በግብፅ ምድር በተሻለችው በራምሴ ምድር ጉልትን ሰጣቸው።
12ዮሴፍም ለአባቱና ለወንድሞቹ ለአባቱም ቤተ ሰዎች ሁሉ እንደ ልጆቻቸው መጠን እህል ሰጣቸው።
13በምድርም ሁሉ እህል አልነበረም፥ ራብ እጅግ ጸንቶአልና፤ ከራብም የተነሣ የግብፅ ምድርና የከነዓን ምድር ተጎዳ።
14ዮሴፍም ከግብፅ ምድርና ከከነዓን ምድር በእህል ሸመት የተገኘውን ብሩን ሁሉ አከማቸ፤ ዮሴፍም ብሩን ወደ ፈርዖን ቤት አስገባው።
15ብሩም በግብፅ ምድርና በከነዓን ምድር አለቀ፤ የግብፅ ሰዎችም ሁሉ ወደ ዮሴፍ መጡ እንዲህ ሲሉ። እንጀራ ስጠን፤ ስለ ምን በፊትህ እንሞታለን? ብሩ አልቆብናልና።
16ዮሴፍም። ከብቶቻችሁን አምጡልኝ፤ ብር ካለቀባችሁ በከብቶቻችሁ ፋንታ እህል እሰጣችኋለሁ አለ።
17ከብቶቻቸውንም ወደ ዮሴፍ አመጡ፥ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው በበጎቻቸውም በላሞቻቸውም በአህዮቻቸውም ፋንታ እህልን ሰጣቸው፤ በዚያች ዓመትም ስለ ከብቶቻቸው ሁሉ ፋንታ እህልን መገባቸው።
18ዓመቱም ተፈጸመ፤ በሁለተኛውም ዓመት ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት። እኛ ከጌታችን አንሰውርም፤ ብሩ በፍጹም አለቀ፥ ከብታችንም ከጌታችን ጋር ነው፤ ከሰውነታችንና ከምድራችን በቀር በጌታችን ፊት አንዳች የቀረ የለም፤
19እኛ በፊትህ ስለ ምን እንሞታለን? ምድራችንስ ስለ ምን ትጠፋለች? እኛንም ምድራችንንም በእህል ግዛን፥ እኛም ለፈርዖን ባሪያዎች እንሁን፥ ምድራችንም ለእርሱ ትሁን፤ እኛ እንድንድን እንዳንሞትም ምድራችንም እንዳትጠፋ ዘር ስጠን።
20ዮሴፍም የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛ፥ የግብፅ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለ ጸናባቸው ርስታቸውን ሸጠዋልና፤ ምድሪቱ ለፈርዖን ሆነች።
21ሕዝቡንም ሁሉ ከግብፅ ዳርቻ አንሥቶ እስከ ሌላው ዳርቻዋ ድረስ ባሪያዎች አደረጋቸው።
22የካህናትን ምድር ብቻ አልገዛም፥ ካህናቱ ከፈርዖን ዘንድ ድርጎ ያገኙ ነበርና፥ ፈርዖንም የሰጣቸውን ድርጎ ይበሉ ነበር፤ ስለዚህም ምድራቸውን አልሸጡም።
23ዮሴፍም ሕዝቡን እንዲህ አለ። እነሆ ዛሬ እናንተንና ምድራችሁን ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁ፤ ዘር ውሰዱና ምድሪቱን ዝሩ፤
24በመከርም ጊዜ ፍሬውን ከአምስት እጅ አንዱን እጅ ለፈርዖን ስጡ፤ አራቱም እጅ ለእናንተ ለራሳችሁ፥ ለእርሻው ዘርና ለእናንተ ምግብ፥ ለቤተ ሰዋችሁና ለሕፃናቶቻችሁም ሲሳይ ይሁን።
25እነርሱም። አንተ አዳነኸን፤ በጌታችን ፊት ሞገስን አናግኝ፥ ለፈርዖንም ባሪያዎች እንሆናለን አሉት።
26ዮሴፍም ለፈርዖን ካልሆነችው ከካህናቱ ምድር በቀር አምስተኛው እጅ ለፈርዖን እንዲሆን በግብፅ ምድር እስከ ዛሬ ድረስ ሕግ አደረጋት።
27እስራኤልም በግብፅ ምድር በጌሤም አገር ተቀመጠ፤ ገዙአትም፥ ረቡ፥ እጅግም በዙ።
28ያዕቆብም በግብፅ ምድር አሥራ ሰባት ዓመት ተቀመጠ፤ የያዕቆብም ሙላው የሕይወቱ ዘመን መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነው።
29የእስራኤልም የሞቱ ቀን ቀረበ፤ ልጁን ዮሴፍንም ጠርቶ እንዲህ አለው። በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ በግብፅ ምድርም እንዳትቀብረኝ ምሕረትንና እውነትን አድርግልኝ፤
30ከአባቶቼም ጋር በተኛሁ ጊዜ ከግብፅ ምድር አውጥተህ ትወስደኛለህ፥ በመቃብራቸውም ትቀብረኛለህ። እርሱም። እንደ ቃልህ አደርጋለሁ አለ።
31እርሱም። ማልልኝ አለው። ዮሴፍም ማለለት፤ እስራኤልም በአልጋው ራስ ላይ ሰገደ።