ምዕራፍ 49
1ያዕቆብም ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አለ። በኋለኛው ዘመን የሚያገኛችሁን እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ።
2እናንት የያዕቆብ ልጆች ተሰብሰቡ፥ ስሙም፤ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ።
3ሮቤል፥ አንተ በኵር ልጄና ኃይሌ፥ የጕብዝናዬም መጀመሪያ ነህ፤ የክብር አለቃና የኃይል አለቃ።
4እንደ ውኃ የምትዋልል ነህ፤ አለቅነት ለአንተ አይሁን፤ ወደ አባትህ መኝታ ወጥተሃልና፤ አረከስኸውም፤ ወደ አልጋዬም ወጣ።
5ስምዖንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው።
6በምክራቸው፥ ነፍሴ፥ አትግባ፤ ከጉባኤአቸውም ጋር፥ ክብሬ፥ አትተባበር፤ በቍጣቸው ሰውን ገድለዋልና፥ በገዛ ፈቃዳቸውም በሬን አስነክሰዋልና።
7ቍጣቸው ርጉም ይሁን፥ ጽኑ ነበርና፤ ኵርፍታቸውም፥ ብርቱ ነበርና፤ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፥ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ።
8ይሁዳ፥ ወንድሞችህ አንተን ያመሰግኑሃል፤ እጅህ በጠላቶችህ ደንደስ ላይ ነው፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ።
9ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፤ ልጄ ሆይ፥ ከአደንህ ወጣህ፤ እንደ አንበሳ አሸመቀ፥ እንደ ሴት አንበሳም አደባ፤ ያስነሣውስ ዘንድ ማን ይችላል?
10በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፥ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፥ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ፤ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል።
11ውርንጫውን በወይን ግንድ ያስራል፥ የአህያይቱንም ግልገል በወይን አረግ፤ ልብሱን በወይን ያጥባል፥ መጎናጸፊያውንም በወይን ደም።
12ዓይኑም ከወይን ይቀላል፤ ጥርሱም ከወተት ነጭ ይሆናል።
13ዛብሎን በባሕር ዳር ይቀመጣል፤ እርሱም ለመርከቦች ወደብ ይሆናል፤ ዳርቻውም እስከ ሲዶና ድረስ ነው።
14ይሳኮር አጥንተ ብርቱ አህያ ነው፥ በበጎች ጕረኖም መካከል ያርፋል።
15ዕረፍትም መልካም መሆንዋን አየ፥ ምድሪቱም የለማች መሆንዋን፤ ትከሻውን ለመሸከም ዝቅ አደረገ፥ በሥራም ገበሬ ሆነ።
16ዳን በወገኑ ይፈርዳል፥ ከእስራኤል ነገድ እንደ አንዱ።
17ዳን በጐዳና ላይ እንደ እባብ ይሆናል፥ በመንገድም እንደ ቀንዳም እባብ፤ ፈረሱን ከሰኮናው ይነክሳል፥ ፈረሰኛም ወደ ኋላው ይወድቃል።
18እግዚአብሔር ሆይ፥ መድኃኒትህን እጠብቃለሁ።
19ጋድን ዘማቾች ይዘምቱበታል፤ እርሱ ግን ተከታትሎ ይዘምትባቸዋል።
20የአሴር እንጀራው ወፍራም ነው፥ ለነገሥታቱም ደስ የሚያሰኝ መብልን ይሰጣል።
21ንፍታሌም የተፈታ ሚዳቋ ነው፤ መልካም ቃልን ይሰጣል።
22ዮሴፍ ትንሹ የፍሬ ዛፍ ነው፥ በምንጭ አጠገብ የሚያፈራ የፍሬ ዛፍ፤ አረጎቹ በቅጥር ላይ ያድጋሉ።
23ቀስተኞች አስቸገሩት፥ ነደፉትም፥ ተቃወሙትም፤
24ነገር ግን ቀስቱ እንደ ጸና ቀረ፤ የእጆቹም ክንድ በያዕቆብ አምላክ እጅ በረታ፥ በዚያው በጠባቂው በእስራኤል ዓምድ፥
25በአባትህ አምላክ እርሱም የሚረዳህ፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ እርሱም የሚባርክህ፥ በሰማይ በረከት ከላይ በሚገኝ፥ በጥልቅም በረከት ከታች በሚሠራጭ፥ በጡትና በማኅፀን በረከት።
26የአባትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ ዘላለማውያን ከሆኑ ከኮረፍቶችም በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ እነርሱም በዮሴፍ ራስ ላይ ይሆናሉ፥ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነው ራስ አናት ላይ።
27ብንያም ነጣቂ ተኵላ ነው፤ የበዘበዘውን በጥዋት ይበላል፥ የማረከውንም በማታ ይካፈላል።
28እነዚህም ሁሉ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው፤ አባታቸው የነገራቸው ይህ ነው፥ ባረካቸውም፤ እያንዳንዳቸውን እንደ በረከታቸው ባረካቸው።
29እንዲህ ብሎም አዘዛቸው። እኔ ወደ ወገኖቼ እሰበሰባለሁ፤ በኬጢያዊ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ጋር ቅበሩኝ፤
30እርስዋም በከነዓን ምድር በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት፥ ባለ ድርብ ክፍል ዋሻ ናት።
31አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ፤ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ከዚያ ተቀበሩ፤ ከዚያም እኔ ልያን ቀበርኋት፤
32እርሻውና በእርስዋ ላይ ያለችው ዋሻ ከኬጢ ልጆች የተገዙ ናቸው።
33ያዕቆብም ትእዛዙን ለልጆቹ ተናግሮ በፈጸመ ጊዜ እግሮቹን በአልጋው ላይ ሰብስቦ ሞተ፥ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ።