ምዕራፍ 1
1ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ።
2ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል።
3እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።
4ክፉዎች እንዲህ አይደሉም፥ ነገር ግን ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ ናቸው።
5ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ፥ ኃጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር አይቆሙም።
6እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃልና፥ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች።