ምዕራፍ 107
1ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
2እግዚአብሔር ያዳናቸው፥ ከጠላቶች እጅ ያዳናቸው ይናገሩ።
3ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከባሕር፥ ከየአገሩ ሰበሰባቸው።
4ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ ተቅበዘበዙ፤ የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም።
5ተራቡ ተጠሙም፥ ነፍሳቸውም በውስጣቸው አለቀች።
6በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው፤
7ወደሚኖሩበት ከተማ ይሄዱ ዘንድ የቀና መንገድን መራቸው።
8ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤
9የተራበችን ነፍስ አጥግቦአልና፥ የተራቈተችንም ነፍስ በበረከት ሞልቶአልና።
10በጨለማ በሞትም ጥላ የተቀመጡ፥ በችግር በብረትም የታሰሩ፤
11የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ዐመፁ፥ የልዑልንም ምክር ስለ ናቁ፥
12ልባቸው በድካም ተዋረደ፤ ታመሙ የሚረዳቸውም አጡ።
13በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ በመከራቸውም አዳናቸው።
14ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥ እስራታቸውንም ሰበረ።
15ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤
16የናሱን ደዶች ሰብሮአልና፥ የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጦአልና።
17ስለ ዓመፃቸው ሰነፉ፥ ስለ ኃጢአታቸውም ተቸገሩ።
18ሰውነታቸው መብልን ሁሉ ተጸየፈች፥ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ።
19በተጨነቁ ጊዜም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው።
20ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም፥ ከጥፋታቸውም አዳናቸው።
21ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመሰግኑ፤
22የምስጋና መሥዋዕትንም ይሠውለት፥ በእልልታም ሥራውን ይንገሩ።
23በመርከቦች ወደ ባሕር የሚወርዱ፥ በታላቅ ውኃ ሥራቸውን የሚሠሩ፥
24እነርሱ የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በጥልቅም ያለችውን ድንቁን አዩ።
25ተናገረ፥ ዐውሎ ነፋስም ተነሣ፥ ሞገድም ከፍ ከፍ አለ።
26ወደ ሰማይ ይወጣሉ ወደ ጥልቅም ይወርዳሉ፤ ነፍሳቸውም በመከራ ቀለጠች።
27ደነገጡ እንደ ስካርም ተንገደገዱ፥ ጥበባቸውም ሁሉ ተዋጠች።
28በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው።
29ዐውሎንም ጸጥ አደረገ፥ ሞገዱም ዝም አለ።
30ዝም ብሎአልና ደስ አላቸው፤ ወደ ፈለጉትም ወደብ መራቸው።
31ለሰው ልጆች ስላደረገው ተአምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ።
32በአሕዛብ ጉባኤ ከፍ ከፍ ያድርጉት፥ በሽማግሌዎችም ሸንጎ ያመስግኑት።
33ወንዞችን ምድረ በዳ፥ የውኃውንም ምንጮች ደረቅ አደረጋቸው፤
34ከተቀመጡባት ክፋት የተነሣ ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት።
35ምድረ በዳን ለውኃ መቆሚያ፥ ደረቁንም ምድር የውኃ ምንጮች አደረገ።
36በዚያም ራብተኞችን አስቀመጠ፥ የሚኖርባትንም ከተማ ሠሩ።
37እርሻዎችንም ዘሩ ወይኖችንም ተከሉ፥ የእህልንም ሰብል አደረጉ።
38ባረካቸውም እጅግም በዙ፤ እንስሶቻቸውንም አላሳነሰባቸውም።
39እነርሱ በችግር በክፋት በጭንቀት ተዋረዱ እያነሱም ሄዱ፤
40በአለቶችም ላይ ኅሣርን፥ አፈሰሰ፥ መንገድም በሌለበት በምድረ በዳ አሳታቸው።
41ችግረኛንም ከችግሩ ረዳው፤ እንደ በጎች መንጋ ወገን አደረገው።
42ቅኖች ያያሉ፥ ደስም ይላቸዋል፤ ኃጢአትም ሁሉ አፍዋን ትዘጋለች።
43ጥበበኛ የሆነና ይህን የሚጠብቅ ማን ነው? እርሱ የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል።