English

ምዕራፍ 118

1እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ናትና።
2ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች የእስራኤል ቤት አሁን ይንገሩ።
3ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች የአሮን ቤት አሁን ይንገሩ።
4ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ አሁን ይንገሩ።
5በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ ሰማኝ አሰፋልኝም።
6እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል?
7እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ እኔም በጠላቶቼ ላይ አያለሁ።
8በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
9በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ ይሻላል።
10አሕዛብ ሁሉ ከበቡኝ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው፤
11መክበቡንስ ከበቡኝ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው፤
12ንብ ማርን እንዲከብብ ከበቡኝ፥ እሳትም በእሾህ ውስጥ እንዲነድድ ነደዱ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው።
13ገፋኸኝ፥ ለመውደቅም ተንገዳገድሁ፤ እግዚአብሔር ግን አገዘኝ።
14ኃይሌም ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም መድኃኒት ሆነልኝ።
15የእልልታና የመድኃኒት ድምፅ በጻድቃን ድንኳን ነው፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች።
16የእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገችኝ፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች።
17አልሞትም በሕይወት እኖራለሁ እንጂ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እናገራለሁ።
18መገሠጽስ እግዚአብሔር ገሠጸኝ፤ ለሞት ግን አልሰጠኝም።
19የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፤ ወደ እነርሱ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
20ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፤ ወደ እርስዋ ጻድቃን ይገባሉ።
21ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ።
22ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፥ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፥
23ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነች፥ ለዓይናችንም ድንቅ ናት።
24እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።
25አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና።
26በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ።
27እግዚአብሔር አምላክ ነው፥ ለእኛም በራልን፤ እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ የበዓሉን መሥዋዕት በገመድ እሰሩት።
28አንተ አምላኬ ነህ አመሰግንህማለሁ። አንተ አምላኬ ነህ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ።
29እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ናትና።