English

ምዕራፍ 147

1እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ መዝሙር መልካም ነውና። ለአምላካችን ምስጋና ያማረ ነው።
2እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይሠራል፥ ከእስራኤልም የተበተኑትን ይሰበስባል።
3ልባቸውን የቈሰሉትን ይፈውሳል፥ ሕማማቸውንም ይጠግናል።
4የከዋክብትንም ብዛት ይቈጥራል፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።
5ጌታችን ታላቅ ነው፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ ለጥበቡም ቍጥር የለውም።
6እግዚአብሔር የዋሃንን ያነሣል፥ ኃጢአተኞችን ግን እስከ ምድር ድረስ ያዋርዳል።
7ለእግዚአብሔር በምስጋና ዘምሩ፥ ለአምላካችንም በመሰንቆ ዘምሩ፤
8ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል ለምድርም ዝናብን ያዘጋጃል፤ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም።
9ለሚጠሩት ለቍራዎች ጫጩቶች ለእንስሶችም ምግባቸውን ይሰጣል።
10የፈረስን ኃይል አይወድድም፥ በሰውም ጭን አይደሰትም።
11እግዚአብሔር በሚፈሩት፥ በምሕረቱም በሚታመኑት ይደሰታል።
12ኢየሩሳሌም ሆይ፥ እግዚአብሔርን አመስግኚ፥
13ጽዮንም ሆይ፥ ለአምላክሽ እልል በዪ፤ የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቶአልና፥ ልጆችንም በውስጥሽ ባርኮአልና።
14በወሰንሽም ሰላምን አደረገ፥ የስንዴንም ስብ አጠገበሽ።
15ነገሩን ወደ ምድር ይሰድዳል፥ ቃሉም እጅግ ፈጥኖ ይሮጣል።
16አመዳዩን እንደ ባዘቶ ይሰጣል፤ ጉሙን እንደ አመድ ይበትነዋል፤
17በረዶውን እንደ ፍርፋሪ ያወርዳል፤ በበረዶውስ ፊት ማን ይቆማል?
18ቃሉን ልኮ ያቀልጠዋል፤ ነፋሱን ያነፍሳል፥ ውኆችንም ያፈስሳል።
19ቃሉን ለያዕቆብ፥ ሥርዓቱንና ፍርዱን ለእስራኤል ይናገራል።
20ለሌሎች አሕዛብ ሁሉ እንዲህ አላደረገም፥ ፍርዱንም አልገለጠላቸውም። ሃሌ ሉያ።