ምዕራፍ 17
1አቤቱ፥ ጽድቄን ስማ ጩኸቴንም አድምጥ፤ በተንኰለኛም ከንፈር ያልሆነውን ጸሎቴን አድምጥ።
2ፍርዴ ከፊትህ ይውጣ፥ ዓይኖችህም በቅንነት ይዩ።
3ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጐበኘኸኝ፤ ፈተንኸኝ፥ ምንም አላገኘህብኝም።
4የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፤ ስለ ከንፈሮችህ ቃል ጭንቅ የሆኑ መንገዶችን ጠበቅሁ።
5እግሮች እንዳይናወጡ አረማመዴን በመንገድህ አጽና።
6አቤቱ፥ ሰምተኸኛልና ወደ አንተ ጠራሁ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ቃሌንም ስማ።
7የሚያምኑህን ከሚቃወሙ በቀኝህ የምታድናቸው፥ ቸርነትህን ድንቅ አድርገህ ግለጠው።
8እንደ ዓይን ብሌን ጠብቀኝ፥ በክንፎችህ ጥላ ሰውረኝ፥
9ከሚያስጨንቁኝ ከኃጢአተኞች፥ ነፍሴንም ከሚከብቡአት ከጠላቶቼ።
10አንጀታቸውን በስብ ቋጠሩ፥ በአፋቸውም ትንቢትን ተናገሩ።
11አሁንም እርምጃችንን ከበቡ፤ ዓይናቸውን ወደ ምድር ዝቅ ዝቅ አደረጉ።
12እርሱ ንጥቂያን እንደሚናፍቅ አንበሳ ተሸጕጦም እንደሚኖር እንደ አንበሳ ደቦል ነው።
13አቤቱ፥ ተነሥ፤ ቀድመህ ወደ ታች ጣለው፤ ነፍሴን ከኃጢአተኛ በሰይፍህ አድናት።
14አቤቱ፥ ከሰዎች፥ እድል ፈንታቸው በሕይወታቸው ከሆነች ከዚህ ዓለም ሰዎች በእጅህ አድነኝ፤ ከሰወርኸው መዝገብህ ሆዳቸውን አጠገብህ፤ ልጆቻቸው ብዙ ናቸው የተረፋቸውንም ለሕፃናቶቻቸው ያተርፋሉ።
15እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ።