ምዕራፍ 22
1አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ቃል ሩቅ ነህ።
2አምላኬ፥ በቀን ወደ አንተ እጠራለሁ፥ አልመለስህልኝም፤ በሌሊትም እንኳ ዕረፍት የለኝም።
3በእስራኤል የተመሰገንህ አንተ ግን በቅድስና ትኖራለህ።
4አባቶቻችን አንተን ተማመኑ፥ ተማመኑ አንተም አዳንሃቸው።
5ወደ አንተ ጮኹ አመለጡም፥ አንተንም ተማመኑ አላፈሩም።
6እኔ ግን ትል ነኝ ሰውም አይደለሁም፤ የሰው ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ።
7የሚያዩኝ ሁሉ ይላገዱብኛል፤ ራሳቸውን እየነቀነቁ በከንፈሮቻቸው እንዲህ ይላሉ።
8በእግዚአብሔር ተማመነ፥ እርሱንም ያድነው፤ ቢወድደውስ ያድነው።
9አንተ ግን ከሆድ አውጥተኸኛልና፥ በእናቴ ጡት ሳለሁም በአንተ ታመንሁ።
10ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ፤ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ።
11ጭንቀት ቀርባለችና የሚረዳኝም የለምና ከእኔ አትራቅ።
12ብዙ በሬዎች ከበቡኝ፥ የሰቡትም ፍሪዳዎች ያዙኝ፤
13እንደ ነጣቂና እንደሚጮኽ አንበሳ በላዬ አፋቸውን ከፈቱ።
14እንደ ውኃ ፈሰስሁ፤ አጥንቶቼም ሁሉ ተለያዩ፤ ልቤ እንደ ሰም ሆነ፥ በአንጀቴም መካከል ቀለጠ።
15ኃይሌ እንደ ገል ደረቀ፥ በጕሮሮዬም ምላሴ ተጣጋ፥ ወደ ሞትም አሸዋ አወረድኸኝ።
16ብዙ ውሾች ከብበውኛልና፤ የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ፤ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ።
17አጥንቶቼ ሁሉ ተቈጠሩ፤ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም።
18ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ።
19አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ፤ አንተ ጕልበቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።
20ነፍሴን ከሰይፍ አድናት፥ ብቻነቴንም ከውሾች እጅ።
21ከአንበሳ አፍ አድነኝ፥ ብቻነቴንም አንድ ቀንድ ካላቸው።
22ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፥ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ።
23እግዚአብሔርን የምትፈሩ፥ አመስግኑት፤ የያዕቆብ ዘር ሁላችሁ፥ አክብሩት፥ የእስራኤልም ዘር ሁላችሁ፥ ፍሩት።
24የችግረኛን ችግር አልናቀምና፥ ቸልም አላለምና፤ ፊቱንም ከእኔ አልሰወረምና፥ ነገር ግን ወደ እርሱ በጮኽሁ ጊዜ ሰማኝ።
25በታላቅ ጉባኤ ምስጋናዬ ከአንተ ዘንድ ነው። እርሱን በሚፈሩት ፊት ስእለቴን እሰጣለሁ።
26ችግረኞች ይበላሉ፥ ይጠግቡማል፤ እግዚአብሔርንም የሚሹት ያመሰግኑታል፤ ልባቸውም ለዘላለም ሕያው ይሆናል።
27የምድር ዳርቻዎች ሁሉ ያስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ይመለሱ፤ የአሕዛብ ነገዶች ሁሉ በፊቱ ይሰግዳሉ።
28መንግሥት ለእግዚአብሔር ነውና፥ እርሱም አሕዛብን ይገዛል።
29የምድር ደንዳኖች ሁሉ ይበላሉ ይሰግዳሉም፤ ወደ መሬት የሚወርዱት ሁሉ በፊቱ ይንበረከካሉ፤ ነፍሴም ስለ እርሱ በሕይወት ትኖራለች።
30ዘሬ ይገዛለታል፤ የምትመጣው ትውልድ ለእግዚአብሔር ትነግረዋለች፤
31ጽድቁንም ለሚወለደው ሕዝብ፥ እግዚአብሔር ያደረገውን ጽድቁን፥ ይነግራሉ።