English

ምዕራፍ 27

1እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው?
2ክፉዎች፥ አስጨናቂዎቼ ጠላቶቼም፥ ሥጋዬን ይበሉ ዘንድ በቀረቡ ጊዜ፥ እነርሱ ተሰናከሉና ወደቁ።
3ሠራዊትም ቢሰፍርብኝ ልቤ አይፈራም፤ ሰልፍም ቢነሣብኝ በዚህ እተማመናለሁ።
4እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።
5በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና።
6እነሆ፥ አሁን በዙሪያ ባሉ በጠላቶቼ ላይ ራሴን ከፍ ከፍ አደረገ፤ በድንኳኑም የእልልታ መሥዋዕትን ሠዋሁ፥ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ እዘምርለትማለሁ።
7አቤቱ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን ቃሌን ስማኝ። ማረኝና አድምጠኝ።
8አንተ ፊቴን እሹት ባልህ ጊዜ። አቤቱ፥ ፊትህን እሻለሁ ልቤ አንተን አለ።
9ፊትህን ከእኔ አትሰውር፥ ተቈጥተህ ከባሪያህ ፈቀቅ አትበል፤ ረዳት ሁነኝ፥ አትጣለኝም፥ የመድኃኒቴም አምላክ ሆይ፥ አትተውኝ።
10አባቴና እናቴ ትተውኛልና፥ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ።
11አቤቱ፥ መንገድህን አስተምረኝ፥ ስለ ጠላቶቼም በቀና መንገድ ምራኝ።
12የሐሰት ምስክሮችና ዓመፀኞች ተነሥተውብኛልና ለጠላቶቼ ፈቃድ አትስጠኝ።
13የእግዚአብሔርን ቸርነት በሕያዋን ምድር አይ ዘንድ አምናለሁ።
14እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።