English

ምዕራፍ 35

1የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ የሚበድሉኝን በድላቸው፥ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው።
2ጥሩርና ጋሻ ያዝ፥ እኔንም ለመርዳት ተነሥ።
3ሰይፍህን ምዘዝ የሚያሳድዱኝንም መንገዳቸውን ዝጋ፤ ነፍሴን። መድኃኒትሽ እኔ ነኝ በላት።
4ነፍሴን የሚሹ ሁሉ ይፈሩ ይጐስቈሉም፤ ክፉትን በእኔ ላይ የሚያስቡ ይፈሩ ወደ ኋላቸውም ይበሉ።
5በነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ ይሁኑ፥ የእግዚአብሔርንም መልአክ ያስጨንቃቸው።
6መንገዳቸው ዳጥና ጨለማ ይሁን፥ የእግዚአብሔርም መልአክ ያሳድዳቸው።
7በከንቱ ያጠፉኝ ዘንድ ወጥመዳቸውን ሸሽገውብኛልና፥ ነፍሴን በከንቱ አበሳጭተዋልና።
8ያላወቁት ወጥመድ ይምጣባቸው፥ የሸሸጉትም ወጥመድ ይያዛቸው፤ በዚህ ወጥመድ ውስጥ ይውደቁ።
9ነፍሴ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፥ በማዳኑም ሐሴት ታደርጋለች።
10አጥንቶቼ ሁሉ እንዲህ ይሉሃል። አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? ችግረኛን ከሚቀማው እጅ፥ ችግረኛንና ድሀውንም ከሚነጥቀው እጅ ታድነዋለህ።
11የክፋት ምስክሮች ተነሡብኝ፥ የማላውቀውንም በእኔ ላይ ተናገሩ።
12ስለ በጎ ክፋትን መለሱልኝ፥ ነፍሴንም ልጆችን አሳጡአት።
13እኔስ እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፥ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤ ጸሎቴም ወደ ብብቴ ተመለሰ።
14ለወዳጄና ለወንድሜ እንደማደርግ አደረግሁ፤ ለእናቱም እንደሚያለቅስ ራሴን ዝቅ ዝቅ አደረግሁ።
15በእኔ ላይ ተሰበሰቡ ደስም አላቸው፤ ግፈኞች በእኔ ላይ ተሰበሰቡ እኔም አላውቅሁም፤ ቀደዱኝ አልተውኝምም።
16ፈተኑኝ በሣቅም ዘበቱብኝ፥ ጥርሳቸውንም በእኔ ላይ አንቀጫቅጩ።
17አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ታይልኛለህ? ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው ብችነቴንም ከአንበሶች አድናት።
18አቤቱ፥ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ እገዛልሃለሁ፥ በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለሁ።
19በግፍ የሚጠሉኝ በላዬ ደስ አይበላቸው፥ በከንቱ የሚጣሉኝም በዓይናቸው አይጣቀሱብኝ።
20ለእኔስ ሰላምን ይናገሩኛልና፥ በቍጣም ሽንገላን ይመክራሉ።
21አፋቸውንም በእኔ ላይ አላቀቁ፤ እሰይ እሰይ፥ ዓይናችን አየው ይላሉ።
22አቤቱ፥ አንተ አየኸው፤ ዝም አትበል፤ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ።
23አምላኬ ጌታዬም፥ ወደ ፍርዴ ተነሥ፥ አቤቱ፥ ፍርዴን አድምጥ።
24አቤቱ አምላኬ፥ እንደ ጽድቅህ ፍረድልኝ፥ በላዬም ደስ አይበላቸው።
25በልባቸው። እሰይ እሰይ፥ ነፍሳችንን ደስ አላት አይበሉ፤ ደግሞም። ዋጥነው አይበሉ።
26በመከራዬ ደስ የሚላቸው ይፈሩ፥ በአንድነትም ይጐስቍሉ፤ በእኔ ላይ የሚታበዩ እፍረትንና ጕስቍልናን ይልበሱ።
27ጽድቄን የሚወድዱአት ደስ ይበላቸው ሐሴትንም ያድርጉ፤ የባሪያውን ሰላም የሚወድድ እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን ዘወትር ይበሉ።
28ምላሴ ጽድቅህን ሁልጊዜም ምስጋናህን ይናገራል።