ምዕራፍ 41
1ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል።
2እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፥ ሕያውም ያደርገዋል፥ በምድር ላይም ያስመሰግነዋል፥ በጠላቶቹም እጅ አያሳልፈውም።
3እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል።
4እኔስ። አቤቱ ማረኝ፤ አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት አልሁ።
5ጠላቶቼም በላዬ ክፋትን ይናገራሉ። መቼም ይሞታል ስሙስ መቼ ይሻራል? ይላሉ።
6እኔን ለማየት ቢገባ ከንቱን ይናገራል፤ ልቡ ኃጢአትን ሰበሰበለት፤ ወደ ሜዳ ይወጣል ይናገራልም።
7በላዬ በመተባበር ጠላቶቼ ሁሉ ይሾካሾኩብኛል፥ በእኔ ላይም ክፋትን ያስባሉ።
8ክፉ ነገር መጣበት፤ ተኝቶአል ከእንግዲህ ወዲህ አይነሣም ይላሉ።
9ደግሞ የሰላሜ ሰው የታመንሁበት እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ።
10አንተ ግን አቤቱ፥ ማረኝ እመልስላቸውም ዘንድ አስነሣኝ።
11ጠላቴ እልል አይልብኝምና ስለዚህ እንደ ወደድኸኝ አወቅሁ።
12እኔን ግን ስለ ቅንነቴ ተቀበልኸኝ፥ በፊትህም ለዘላለም አጸናኸኝ።
13ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአሔር ይባረክ። አሜን አሜን።