ምዕራፍ 46
1አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።
2ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።
3ውኆቻቸው ጮኹ ተናወጡም፥ ተራሮችም ከኃይሉ የተነሣ ተናወጡ።
4የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ፤ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ።
5እግዚአሔር በመካከልዋ ነው አትናወጥም፥ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ይረዳታል።
6አሕዛብ ተናወጡ መንግሥታትም ተመለሱ፤ እርሱ ቃሉን ሰጠ፥ ምድርም ተንቀጠቀጠች።
7የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።
8የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተኣምራት እንድታዩ ኑ።
9እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነት ይሽራል። ቀስትን ይሰብራል፥ ጦርንም ይቈርጣል በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።
10ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤ በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።
11የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።