ምዕራፍ 48
1እግዚአብሔር ትልቅ ነው፤ በአምላካችን ከተማ በተቀደሰ ተራራ ምስጋናው ብዙ ነው።
2በሰሜን ወገን በመልካም ስፍራ የቆመ የምድር ሁሉ ደስታ የጽዮን ተራራ ነው፤ እርሱም የትልቁ ንጉሥ ከተማ ነው።
3እግዚአብሔር በአዳራሾችዋ መጠጊያ ሆኖ ይታወቃል።
4እነሆ፥ ነገሥታት ተከማችተው በአንድነት መጥተዋል።
5እነርሱስ አይተው ተደነቁ፥ ደነገጡ፥ ታወኩ።
6መንቀጥቀጥ እንደ ወላድ ምጥ በዚያ ያዛቸው።
7በኃይለኛ ነፋስ የተርሴስን መርከቦች ትሰብራለህ።
8እንደ ሰማን እንዲሁ አየን በሠራዊት ጌታ ከተማ፥ በአምላካችን ከተማ፤ እግዚአብሔር ለዘላለም ያጸናታል።
9አምላክ ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ምሕረትህን ተቀበልን።
10አምላክ ሆይ፥ እንደ ስምህ እንዲሁም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስጋናህ ነው፤ ቀኝህ ጽድቅን የተሞላች ናት።
11አቤቱ፥ ስለ ፍርድህ የጽዮን ተራራ ደስ ይበለው፥ የአይሁድም ሴት ልጆች ሐሤት ያድርጉ።
12ጽዮንን ክበቡአት፥ በዙሪያዋም ተመላለሱ፥ ግንቦችዋንም ቍጠሩ፤
13በብርታትዋ ልባችሁን አኑሩ፤ አዳራሽዋን አስቡ፤ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ።
14ለዓለምና ለዘላለም ይህ አምላካችን ነው፥ እርሱም ለዘላለም ይመራናል።