ምዕራፍ 5
1አቤቱ፥ ቃሌን አድምጥ፥ ጩኸቴንም አስተውል፤
2የልመናዬን ቃል አድምጥ፥ ንጉሤና አምላኬ ሆይ፥ አቤቱ፥ ወደ አንተ እጸልያለሁና።
3በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ፥ በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ፥ እጠብቃለሁም።
4አንተ በደልን የማትወድድ አምላክ ነህና፤ ክፉ ከአንተ ጋር አያድርም።
5በከንቱ የሚመኩ በዓይኖችህ ፊት አይኖሩም፤ ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ጠላህ።
6ሐሰትን የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ፤ ደም አፍሳሹንና ሸንጋዩን ሰው እግዚአብሔር ይጸየፋል።
7እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ።
8አቤቱ፥ ስለ ጠላቶቼ በጽድቅህ ምራኝ፤ መንገዴን በፊትህ አቅና።
9በአፋቸው እውነት የለምና፥ ልባቸውም ከንቱ ነው፤ ጕሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ይሸነግላሉ።
10አቤቱ፥ ፍረድባቸው፥ በምክራቸውም ይውደቁ፤ ስለ ክፋታቸውም ብዛት አሳድዳቸው፥ እነርሱ ዐምፀውብሃልና።
11በአንተ የሚታመኑት ሁሉ ግን ደስ ይላቸዋል፤ ለዘላለሙ ደስ ይላቸዋል፥ እነርሱንም ትጠብቃለህ፤ ስምህንም የሚወድዱ ሁሉ በአንተ ይመካሉ።
12አንተ ጻድቁን ትባርከዋለህና፤ አቤቱ፥ እንደ ጋሻ በሞገስ ከለልኸን።