English

ምዕራፍ 62

1ነፍሴ ለእግዚአብሔር የምትገዛ አይደለችምን? መድኃኒቴ ከእርሱ ዘንድ ናትና።
2እርሱ አምላኬ መድኃኒቴም ነውና፤ እርሱ መጠጊያዬ ነው፥ እጅግም አልታወክም።
3እስከ መቼ በሰው ላይ ትቆማላችሁ? እናንተ ሁላችሁ እንዳዘነበለ ግድግዳ እንደ ፈረሰም ቅጥር ትገድላላችሁ።
4ነገር ግን ክብሬን ይሽሩ ዘንድ መከሩ፥ ሐሰትንም ይወድዳሉ፤ በአፋቸው ይባርካሉ፥ በልባቸውም ይረግማሉ።
5ነገር ግን፥ ነፍሴ ሆይ፥ አንቺ ለእግዚአብሔር ተገዢ፥ ተስፋዬ ከእርሱ ዘንድ ናትና።
6እርሱ አምላኬ መድኃኒቴም ነውና፤ እርሱ መጠጊያዬ ነው፤ አልታወክም።
7መድኃኒቴና ክብሬ በእግዚአብሔር ነው፤ የረድኤቴ አምላክ ተስፋዬም እግዚአብሔር ነው።
8የሕዝብ ማኅበር ሁላችሁ፥ በእርሱ ታመኑ፥ ልባችሁንም በፊቱ አፍስሱ፤ እግዚአብሔር ረዳታችን ነው።
9ነገር ግን የሰው ልጆች ከንቱ ናቸው፥ የሰው ልጆችም ሐሰተኞች ናቸው፤ በሚዛንም ይበድላሉ፥ እነርሱስ በፍጹም ከንቱ ናቸው።
10ዓመፃን ተስፋ አታድርጉ፥ ቅሚያንም አትተማመኑት፤ ባለጠግነት ቢበዛ ልባችሁ አይኵራ።
11እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናገረ፥ እኔም ይህን ብቻ ሰማሁ፤ ኃይል የእግዚአብሔር ነው፥
12አቤቱ፥ ምሕረትም ያንተ ነው፤ አንተ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ፍዳውን ትሰጣለህና።