ምዕራፍ 71
1አቤቱ፥ አንተን ታመንሁ፤ ለዘላለም አልፈር።
2በጽድቅህ አስጥለኝ ታደገኝም፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድነኝም።
3በጠንካራ ቦታ ታድነኝ ዘንድ አምላክና መሸሸጊያ ሁነኝ፤ ኃይሌ መጠጊያዬ አንተ ነህና።
4አምላኬ፥ ከኃጢአተኛ እጅ፥ ከዓመፀኛና ከግፈኛም እጅ አድነኝ።
5አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፥ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና።
6ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ፥ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤ ሁልጊዜም ዝማሬዬ ለአንተ ነው።
7ለብዙዎች መደነቂያ ሆንሁ፤ አንተ ግን ብርቱ መጠጊያዬ ነህ።
8አፌን ምስጋና ምላ ሁልጊዜ ክብርህንና ግርማህን እዘምር ዘንድ።
9በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፥ ጕልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ።
10ጠላቶቹ በላዬ ተናግረዋልና፤ ነፍሴንም የሚሹአት በአንድነት ተማክረዋልና፥ እንዲህም አሉ።
11እግዚአብሔር ትቶታል፤ የሚያድነው የለምና ተከትላችሁ ያዙት።
12አምላክ ሆይ፥ ከእኔ አትራቅ፤ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።
13ነፍሴን የሚቃወሙአት ይፈሩ ይጥፉም፥ ጕዳቴንም የሚፈልጉ እፍረትንና ኃሣርን ይልበሱ።
14እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፥ በምስጋናህም ሁሉ ላይ እጨምራለሁ።
15ሥራን አላውቅምና አፌ ጽድቅህን ሁልጊዜም ማዳንህን ይናገራል።
16በእግዚአብሔር ኃይል እገባለሁ፤ አቤቱ፥ ጽድቅህን ብቻ አስባለሁ።
17አምላኬ፥ ከታናሽነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እስከ ዛሬም ተአምራትህን እነግራለሁ።
18እስካረጅም እስክሸመግልም ድረስ፥ ለሚመጣ ትውልድም ሁሉ ክንድህን ኃይልህንም ጽድቅህንም እስክነግር ድረስ፥ አቤቱ፥ አትተወኝ።
19አቤቱ፥ እስከ አርያም ታላላቅ ነገሮችን አደረግህ፤ አምላክ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?
20ብዙ ጭንቀትንና መከራን አሳይተኸኛልና፥ ተመለስህ ሕያውም አደረግኸኝ፤ ከምድር ጥልቅም እንደ ገና አወጣኸኝ።
21ጽድቅህንም አብዛው፥ ተመልሰህም ደስ አሰኘኝ፥ ከጥልቅም እንደ ገና አወጣኸኝ።
22እኔም በበገና ስለ እውነትህ አመሰግንሃለሁ፤ የእስራኤል ቅዱስ አምላክ ሆይ፥ በመሰንቆ እዘምርልሃለሁ።
23ዝማሬን ባቀርብሁልህ ጊዜ ከንፈሮቼ ደስ ይላቸዋል፥ አንተ ያዳንሃትም ነፍሴ።
24ጕዳቴን የሚሹ ባፈሩና በተነወሩ ጊዜ አንደበቴ ደግሞ ሁልጊዜ ጽድቅህን ይናገራል።