English

ምዕራፍ 74

1አቤቱ፥ ስለ ምን ለዘወትር ጣልኸኝ? በማሰማርያህ በጎች ላይስ ቍጣህን ስለ ምን ተቈጣህ?
2አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን፥ የተቤዤሃትንም የርስትህን በትር፥ በእርስዋ ያደርህባትን የጽዮንን ተራራ አስብ።
3ጠላት በቅዱሳንህ ላይ እንደ ከፋ መጠን፥ ሁልጊዜም በትዕቢታቸው ላይ እጅህን አንሣ።
4ጠላቶችህ በበዓል መካከል ተመኩ፤ የማያውቁትንም ምልክት ምልክታቸው አደረጉ።
5እንደ ላይኛው መግቢያ ውስጥ በዱር እንዳሉም እንጨቶች፥ በመጥረቢያ በሮችዋን ሰበሩ።
6እንዲሁ በመጥረቢያና በመዶሻ ሰበሩአት።
7መቅደስህን በእሳት አቃጠሉ፤ የስምህንም ማደሪያ በምድር ውስጥ አረከሱ።
8አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው። ኑ፥ የእግዚአብሔርን በዓሎች ከምድር እንሻር አሉ።
9ምልክታችንን አናይም ከእንግዲህ ወዲህም ነቢይ የለም፤ እስከ መቼ እንዲኖር የሚያውቅ በኛ ዘንድ የለም።
10አቤቱ፥ ጠላት እስከ መቼ ይሳደባል? ስምህን ጠላት ሁልጊዜ ያቃልላልን?
11ቀኝህንም በብብትህ መካከል፥ እጅህንም ፈጽመህ ለምን ትመልሳለህ?
12እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ።
13አንተ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት፤ አንተ የእባቦችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ።
14አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው።
15አንተ ምንጮቹንና ፈሳሾቹን ሰነጠቅህ፤ አንተ ሁልጊዜ የሚፈስሱትን ወንዞች አደረቅህ።
16ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው፤ አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ።
17አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ፤ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ።
18ይህን ፍጥረትህን አስብ። ጠላት እግዚአብሔርን ተላገደ፥ ሰነፍ ሕዝብም ስሙን አስቈጣ።
19የምትገዛልህን ነፍስ ለአራዊት አትስጣት፤ የችግረኞችህን ነፍስ ለዘወትር አትርሳ።
20ወደ ኪዳንህ ተመልከት፥ የምድር የጨለማ ስፍራዎች በኅጥኣን ቤቶች ተሞልተዋልና።
21ችግረኛ አፍሮ አይመለስ፤ ችግረኛና ምስኪን ስምህን ያመሰግናሉ።
22አቤቱ፥ ተነሥ በቀልህንም ተበቀል፤ ሰነፎች ሁልጊዜም የተላገዱህን አስብ።
23የባሪያዎችህን ቃል አትርሳ፤ የጠላቶችህ ኵራት ሁልጊዜ ወደ አንተ ይወጣል።