English

ምዕራፍ 76

1እግዚአብሔር በይሁዳ ታወቀ፥ ስሙም በእስራኤል ታላቅ ነው።
2ስፍራው በሳሌም፥ ማደሪያውም በጽዮን ነው።
3በዚያም የቀስትን ኃይል፥ ጋሻን ሰይፍን ሰልፍንም ሰበረ፤ በዚያም ቀንዶችን ሰበረ።
4አንተ በዘላለም ተራሮች ሆነህ በድንቅ ታበራለህ።
5ልበ ሰነፎች ሁሉ ደነገጡ፥ እንቅልፋቸውንም አንቀላፉ፤ ባለጠጎች ሁሉ በእነርሱ እጅ ምንም አላገኙም።
6የያዕቆብ አምላክ ሆይ፥ ከተግሣጽህ የተነሣ ፈረሰኞች ሁሉ አንቀላፉ።
7አንተ ግን፥ አንተ ግሩም ነህ፤ ቍጣህን ማን ይቃወማል?
8ፍርድን ከሰማይ አሰማህ፤ ምድር ፈራች ዝምም አለች፥
9ልበ የዋሃን ያድን ዘንድ እግዚአብሔር ለፍርድ በተነሣ ጊዜ።
10ሰው በፈቃዱ ያመሰግንሃልና፥ ከሕሊናቸው ትርፍም በዓልህን ያደርጋሉ።
11ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ስእለትን ክፈሉ፤ በዙሪያው ያሉ ሁሉ እጅ መንሻን ለሚያስፈራው ያገባሉ።
12የመኳንንትን ነፍስ ያወጣል፤ በምድርም ነገሥታት ዘንድ ያስፈራል።