English

ምዕራፍ 94

1እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው። የበቀል አምላክ ተገለጠ።
2የምድር ፈራጅ ሆይ፥ ከፍ ከፍ በል፤ ለትዕቢተኞች ፍዳቸውን ክፈላቸው።
3አቤቱ፥ ኃጢአተኞች እስከ መቼ? ኃጢአተኞች እስከ መቼ ይጓደዳሉ?
4ይከራከራሉ፥ ዓመፃንም ይናገራሉ፤ ዓመፃንም የሚያደርጉ ሁሉ ይናገራሉ።
5አቤቱ፥ ሕዝብን አዋረዱ፥ ርስትህንም አስቸገሩ።
6ባልቴቲቱንና ድሀ አደጉን ገደሉ፥ ስደተኛውንም ገደሉ።
7እግዚአብሔር አያይም፥ የያዕቆብ አምላክ አያስተውልም አሉ።
8የሕዝብ ደንቆሮች ሆይ፥ አስተውሉ፤ ሰነፎችማ መቼ ይጠበባሉ?
9ጆሮን የተከለው አይሰማምን? ዓይንን የሠራው አያይምን?
10አሕዛብንስ የሚገሥጸው፥ ለሰውም እውቀት የሚያስተምረው እርሱ አይዘልፍምን?
11የሰዎች አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ያውቃል።
12-
13ለኃጢአተኛ ጕድጓድ እስኪቈፈር ድረስ ከክፉዎች ዘመናት ይወገድ ዘንድ፥ አቤቱ፥ አንተ የገሠጽኸው ሕግህንም ያስተማርኸው ሰው ምስጉን ነው።
14እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፥ ርስቱንም አይተውምና
15ፍርድ ወደ ጽድቅ እስኪመልስ ድረስ ልበ ቅኖችም ሁሉ ይከተሉአታል።
16በክፉዎች ላይ ለእኔ የሚቆም ማን ነው? ዓመፃንስ በሚያደርጉ ላይ ለእኔ የሚከራከር ማን ነው?
17እግዚአብሔር የረዳኝ ባይሆን ነፍሴ ለጥቂት ጊዜ በሲኦል ባደረች ነበር።
18እግሮቼ ተሰናከሉ ባልሁ ጊዜ፥ አቤቱ፥ ምሕረትህ ረዳኝ።
19አቤቱ፥ ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።
20በሕግ ላይ ዓመፅን የሚሠራ የዓመፅ ዙፋን ከአንተ ጋር አንድ ይሆናልን?
21የጻድቅን ነፍስ ያደቡባታል፥ በንጹሕ ደምም ይፈርዳሉ።
22እግዚአብሔር መጠጊያ ሆነኝ፥ አምላኬ የተስፋዬም ረዳት ነው።
23እንደ በደላቸውም እንደ ክፋታቸውም ፍዳቸውን ይከፍላቸዋል፥ አምላካችን እግዚአብሔርም ያጠፋቸዋል።