ምዕራፍ 98
1ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፥ እግዚአብሔር ተኣምራትን አድርጎአልና፤ ቀኙ የተቀደሰም ክንዱ ለእርሱ ማዳን አደረገ።
2እግዚአብሔር ማዳኑን አስታወቀ፥ በአሕዛብም ፊት ጽድቁን ገለጠ።
3ለያዕቆብ ምሕረቱን ለእስራኤልም ቤት እውነቱን አሰበ፤ የምድር ዳርቻዎች ሁሉ የአምላካችንን ማዳን አዩ።
4ምድር ሁሉ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፤ አመስግኑ፥ ደስ ይበላችሁ፥ ዘምሩም።
5ለእግዚአብሔር በመሰንቆ፥ በመሰንቆና በዝማሬ ድምፅ ዘምሩ።
6በዋሽንትና በመለከት ድምፅ በንጉሥ በእግዚአብሔር ፊት እልል በሉ።
7ባሕርና ሞላዋ፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ይናወጡ።
8ወንዞችም በአንድነት በእጅ ያጨብጭቡ፤ ተራሮች ደስ ይበላቸው፥ በምድር ሊፈርድ ይመጣልና።
9ለዓለምም በጽድቅ ለአሕዛብም በቅንነት ይፈርዳል።