ምዕራፍ 27
1ቀን የሚያመጣውን ምን እንደ ሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ።
2ሌላ ያመስግንህ እንጂ አፍህ አይደለም፤ ባዕድ ሰው እንጂ ከንፈርህ አይደለም።
3ድንጋይ ከባድ ነው አሸዋም ሸክሙ ጽኑ ነው፤ ከሁለቱ ግን የሰነፍ ቍጣ ይከብዳል።
4ቍጣ ምሕረት የሌለው ነው፥ መዓትም እንደ ጎርፍ ነው፤ በቅንዓት ፊት ግን ማን ይቆማል?
5የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል።
6የወዳጅ ማቍሰል የታመነ ነው፤ የጠላት መሳም ግን የበዛ ነው።
7የጠገበች ነፍስ የማር ወላላ ትረግጣለች፤ ለተራበች ነፍስ ግን የመረረ ነገር ሁሉ ይጣፍጣታል።
8ስፍራውን የሚተው ሰው፤ ቤቱን ትቶ እንደሚበርር ወፍ ነው።
9ሽቱና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ እንዲሁ ነፍስ በወዳጁ ምክር ደስ ይላታል።
10ወዳጅህንና የአባትህን ወዳጅ አትተው፤ በመከራህም ቀን ወደ ወንድምህ ቤት አትግባ፤ የቀረበ ወዳጅ ከራቀ ወንድም ይሻላል።
11ልጄ ሆይ፥ ጠቢብ ሁን፥ ልቤንም ደስ አሰኘው፥ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ።
12ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ።
13ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥ ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው።
14ባልንጀራውን በታላቅ ቃል ማለዳ የሚባርክ ሰው እንደሚራገም ያህል ነው።
15በዝናብ ቀን የሚያንጠባጥብ ቤትና ጠበኛ ሴት አንድ ናቸው፤
16እርስዋንም መከልከል ነፍስን መከልከልና ዘይትን በቀኝ እጅ መጨበጥ ነው።
17ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል።
18በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል፥ ጌታውንም የሚጠብቅ ይከብራል።
19ፊት በውኃ ላይ ለፊት እንደሚታይ፥ እንዲሁ የሰው ልብ ለሰው ይታያል።
20ሲኦልና ጥፋት እንዳይጠግቡ፥ እንዲሁ የሰው ዓይን አይጠግብም።
21ብር በከውር ወርቅም በማቅለጫ ይፈተናል፤ ሰውም በሚያመሰገኑት ሰዎች አፍ ይፈተናል።
22ሰነፍን በሙቀጫ ውስጥ ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠው፥ ስንፍናው ከእርሱ አይርቅም።
23የበጎችህን መልክ አስተውለህ እወቅ፥ በከብቶችህም ላይ ልብህን አኑር፤
24ባለጠግነት ለዘላለም አይኖርምና፥ ዘውድም ለትውልድ ሁሉ አይጸናምና።
25ደረቅ ሣር በታጨደ ጊዜ፥ አዲስ ለምለም በታየ ጊዜ፥ ከተራራውም ቡቃያ በተሰበሰበ ጊዜ፥
26በጎች ለልብስህ ፍየሎችም የእርሻ ዋጋ ይሆናሉ።
27ለሲሳይህ ለቤተ ሰቦችህም ሲሳይ ለገረዶችህም ምግብ የፍየል ወተት ይበቃል።