ምዕራፍ 4
1ቦዔዝም ወደ ከተማይቱ በር አደባባይ ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። እነሆም፥ ቦዔዝ ስለ እርሱ ይናገር የነበረው የቅርብ ዘመድ ሲያልፍ ቦዔዝ። አንተ ቀርበህ በዚህ ተቀመጥ አለው። እርሱም ቀረብ ብሎ ተቀመጠ። - አንተ ቀርበህ በዚህ ተቀመጥ አለው።
2ቦዔዝም ከከተማይቱ ሽማግሌዎች አሥር ሰዎች ጠርቶ። በዚህ ተቀመጡ አላቸው።
3እነርሱም ተቀመጡ። ቦዔዝም የቅርብ ዘመዱን። ከሞዓብ ምድር የተመለሰችው ኑኃሚን የወንድማችንን የአቤሜሌክን ጢንጦ ትሸጣለች።
4እኔም በዚህ በተቀመጡት በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊት እንድትገዛው አስታውቅህ ዘንድ አሰብሁ። መቤዠት ብትወድድ ተቤዠው፤ መቤዠት ባትወድድ ግን ከአንተ በቀር ሌላ ወራሽ የለምና፥ እኔም ከእአንተ በኋላ ነኝና እንዳውቀው ንገረኝ አለው። እርሱም። እቤዠዋለሁ አለው።
5ቦዔዝም። እርሻውን ከኑኃሚን እጅ በምትገዛበት ቀን፥ ለሞተው በርስቱ ስሙን እንድታስነሣለት ከምዋቹ ሚስት ከሞዓባዊቱ ከሩት ደግሞ ትገዛለህ አለ።
6የቅርብ ዘመዱም። የራሴን ርስት እንዳላበላሽ መቤዠት አልችልም፤ እኔ መቤዠቱን አልችልምና አንተ ከእኔ መቤዠቱን ውሰደው አለ።
7በጥንት ጊዜም፥ ማንም ቢሸጥ ቢለውጥም፥ ነገሩን ለማጽናት ሰው ጫማውን እንዲያወልቅ ለባልንጀራውም እንዲሰጠው በእስራኤል ዘንድ ልማድ ነበረ። ይህም በእስራኤል ምስክር ነበረ።
8የቅርብ ዘመዱም ቦዔዝን። አንተ ግዛው አለው፤ ጫማውንም አወለቀ።
9ቦዔዝም ሽማግሌዎችንና ሕዝቡን ሁሉ። ለአቤሜሌክና ለኬሌዎን ለመሐሎንም የነበረውን ሁሉ ከኑኃሚን እጅ እንደ ገዛሁ እናንተ ዛሬ ምስክሮች ናችሁ።
10ደግሞም የምዋቹ ስም ከወንድሞቹ መካከል ከአገሩም ደጅ እንዳይጠፋ፥ የምዋቹን ስም በርስቱ ላይ እንዳስነሣ የመሐሎንን ሚስት ሞዓባዊቱን ሩትን ሚስት ትሆነኝ ዘንድ ወሰድሁአት፤ እናንተም ዛሬ ምስክሮች ናችሁ አላቸው።
11በከተማይቱ በር አደባባይም የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ሽማግሌዎቹም። እኛ ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ይህችን ወደ ቤትህ የምትገባውን ሴት የእስራኤልን ቤት እንደ ሠሩ እንደ ሁለቱ እንደ ራሔልና እንደ ልያ ያድርጋት፤ አንተም በኤፍራታ ባለ ጠጋ ሁን፥ ስምህም በቤተ ልሔም ይጠራ።
12ቤትህም እግዚአብሔር ከዚህች ቈንጆ ከሚሰጥህ ዘር ትዕማር ለይሁዳ እንደ ወለደችው እንደ ፋሬስ ቤት ይሁን አሉት።
13ቦዔዝም ሩትን ወሰደ፥ ሚስትም ሆነችው፤ ደረሰባትም፥ እግዚአብሔርም ፅንስ ሰጣት፥ ወንድ ልጅም ወለደች።
14ሴቶችም ኑኃሚንን። ዛሬ ዋርሳ ያላሳጣሽ እግዚአብሔር ይባረክ፤ ስሙም በእስራኤል ይጠራ።
15ከሰባትም ወንዶች ልጆች ይልቅ ለአንቺ ከምትሻል ከምትወድድሽ ምራት ተወልዶአልና ሰውነትሽን ያሳድሰዋል፥ በእርጅናሽም ይመግብሻል አሉአት።
16ኑኃሚንም ሕፃኑን ወሰደች አቀፈችውም፥ ሞግዚትም ሆነችው።
17ሴቶችም ጎረቤቶችዋ፥ ለኑኃሚን ወንድ ልጅ ተወለደላት እያሉ ስም አወጡለት፤ ስሙንም ኢዮቤድ ብለው ጠሩት። እርሱም የዳዊት አባት የእሴይ አባት ነው።
18የፋሬስም ትውልድ ይህ ነው፤ ፋሬስ ኤስሮምን ወለደ፥
19ኤስሮምም አራምን ወለደ፥ አራምም አሚናዳብን ወለደ፥
20አሚናዳብም ነአሶንን ወለደ፥ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፥
21ሰልሞንም ቦዔዝን ወለደ፥
22ቦዔዝም ኢዮቤድን ወለደ፥ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፥ እሴይም ዳዊትን ወለደ።