English

ምዕራፍ 10

1የሳባም ንግሥት በእግዚአብሔር ስም የወጣለትን የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች።
2በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፤ ወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው።
3ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሊፈታላት ያልቻለውና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም።
4የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፥
5የማዕዱንም መብል፥ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም አሠራር አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፥ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ነፍስ አልቀረላትም።
6ንጉሡንም አለችው። ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው።
7እኔም መጥቼ በዓይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር፤ እነሆም፥ እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል።
8በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችህና እነዚህ ባሪያዎችህ ምስጉኖች ናቸው።
9አንተን የወደደ፥ በእስራኤልም ዙፋን ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን፤ እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘላለም ወድዶታልና ስለዚህ ጽድቅና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ንጉሥ አድርጎ አስነሣህ።
10ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ የሽቱ ብዛት ከዚያ ወዲያ አልመጣም ነበር።
11ከኦፊርም ወርቅ ያመጡ የኪራም መርከቦች እጅግ ብዙ የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቍ ከኦፊር አመጡ።
12ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለንጉሡ ቤት መከታ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና አደረገ፤ እስከ ዛሬም ድረስ እንደዚያ ያለ የሰንደል እንጨት ከቶ አልመጣም አልታየምም።
13ንጉሡም ሰሎሞን፥ በገዛ እጁ ከሰጣት ሌላ፥ የወደደችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ለሳባ ንግሥት ሰጣት፤ እርስዋም ተመልሳ ከባሪያዎችዋ ጋር ወደ ምድርዋ ሄደች።
14
15ግብርም የሚያስገብሩ ሰዎች ነጋዴዎችም የዓረብም ነገሥታት ሁሉ የምድርም ሹማምት ከሚያወጡት ሌላ፥ በየዓመቱ ለሰሎሞን የሚመጣለት የወርቅ ሚዛን ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበረ።
16ንጉሡም ሰሎሞን ከጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ አላበሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበረ።
17ከጥፍጥፍም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት ምናን ነበረ፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አኖራቸው።
18ንጉሡም ደግሞ ከዝሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፥ በጥሩም ወርቅ ለበጠው።
19ወደ ዙፋንም የሚያስሄዱ ስድስት እርከኖች ነበሩ፤ በስተ ኋላውም ያለው የዙፋኑ ራስ ክብ ነበረ፤ በዚህና በዚያ በመቀመጫው አጠገብ ሁለት የክንድ መደገፊያዎች ነበሩበት፥ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር።
20በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ አሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በመንግሥታት ሁሉ እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም።
21ንጉሡም ሰሎሞን የሚጠጣበት ዕቃ ሁሉ ወርቅ ነበረ፥ የሊባኖስ ዱር የተባለውም ቤት ዕቃ ሁሉ ጥሩ ወርቅ እንጂ ብር አልነበረም። በሰሎሞን ዘመን ብር ከቶ አይቈጠርም ነበር።
22ለንጉሡም ከኪራም መርከቦች ጋር የተርሴስ መርከቦች ነበሩት፤ በሦስት በሦስት ዓመትም አንድ ጊዜ የተርሴስ መርከቦች ወርቅና ብር፥ የዝሆንም ጥርስ፥ ዝንጀሮና ዝንጕርጕር ወፍ ይዘው ይመጡ ነበር።
23ንጉሡም ሰሎሞን በባለጠግነትና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ በልጦ ነበር።
24ምድርም ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረለትን ጥበቡን ይሰማ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ይመኝ ነበር።
25ከእነርሱም እያንዳንዱ በዓመቱ በዓመቱ ገጸ በረከቱን፥ የብርና የወርቅ ዕቃ፥ ልብስና የጦር መሣሪያ፥ ሽቱም፥ ፈረሶችና በቅሎች እየያዘ ይመጣ ነበር።
26ሰሎሞንም ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፤ አንድ ሺህ አራት መቶ ሰረገሎች፥ አሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፥ በሰረገሎችም ከተሞች ከንጉሡም ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው።
27ንጉሡም ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ።
28ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አገር አስመጣ፤ የንጉሡም ነገዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር።
29አንዱም ሰረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ አምሳ ብር ከግብጽ ይወጣ ነበር። እንዲሁም ለኬጢያውያንና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ በእጃቸው ያወጡላቸው ነበር። a