ምዕራፍ 16
1የእግዚአብሔርም ቃል በባኦስ ላይ እንዲህ ብሎ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ።
2እኔ ከመሬት አስነሥቼ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ አድርጌሃለሁ፤ አንተ ግን በኢዮርብዓም መንገድ ሄደሃል፥ በኃጢአታቸውም ያስቈጡኝ ዘንድ ሕዝቤን እስራኤልን አስተሃቸዋል።
3ስለዚህም፥ እነሆ፥ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ እጠርጋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርጋለሁ።
4ከባኦስም ወገን በከተማይቱ ውስጥ የሚሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በሜዳውም የሚሞተውን የሰማይ ወፎች ይበሉታል።
5የቀረውም የባኦስ ነገር፥ ሥራውና ጭከናውም፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
6ባኦስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በቴርሳም ተቀበረ፤ ልጁም ኤላ በፋንታው ነገሠ።
7በእጁም ሥራ ያስቈጣው ዘንድ፥ እንደ ኢዮርብዓም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ስላደረገው ክፋት ሁሉ እርሱንም ስለ ገደለው፥ የእግዚአብሔር ቃል በባኦስና በቤቱ ላይ ወደ አናኒ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ኢዩ መጣ።
8በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሀያ ስድስተኛው ዓመት የባኦስ ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ በቴርሳ ሁለት ዓመት ነገሠ።
9የእኩሌቶቹም ሰረገሎች አለቃ ዘምሪ ተማማለበት፤ ኤላም በቴርሳ ነበረ፥ በቴርሳም በነበረው በቤት አሽከሮች አለቃ በኦሳ ቤት ይሰክር ነበር።
10በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሀያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ ገብቶ መታው ገደለውም፥ በፋንታውም ነገሠ።
11ንጉሥም በሆነ ጊዜ፥ በዙፋኑም በተቀመጠ ጊዜ፥ የባኦስን ቤት ሁሉ መታ፤ ከዘመዶችና ከወዳጆች ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ አልቀረም።
12
13ባኦስና ልጁ ኤላ ስለ ሠሩት ኃጢአት ሁሉ፥ በምናምንቴም ሥራቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ስለ አሳቱበት ኃጢአት፥ በነቢዩ በኢዩ እጅ በባኦስ ላይ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዘምሪ የባኦስን ቤት ሁሉ እንዲሁ አጠፋ።
14የቀረውም የኤላ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
15በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሀያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሰባት ቀን ነገሠ። ሕዝቡም በፍልስጥኤም አገር የነበረው ገባቶንን ከብበው ነበር።
16ከተማይቱንም ከብበው የነበሩ ሕዝብ ዘምሪ እንደ ዐመፀ፥ ንጉሡንም እንደ ገደለ ሰሙ፤ እስራኤልም ሁሉ በዚያ ቀን በሰፈሩ ውስጥ የሠራዊቱን አለቃ ዘንበሪን አነገሡ።
17ዘንበሪም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከገባቶን ወጥተው ቴርሳን ከበቡ።
18ዘምሪም ከተማይቱ እንደ ተያዘች ባየ ጊዜ ወደ ንጉሡ ቤት ግንብ ውስጥ ገባ፥ የንጉሡንም ቤት በራሱ ላይ በእሳት አቃጠለ፤
19ስላደረገውም ኃጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት ኃጢአት፥ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርጎአልና፥ በኢዮርብዓምም መንገድ ሄዶአልና ሞተ።
20የቀረውም የዘምሪ ነገር፥ ያደረገውም ዐመፅ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
21በዚያም ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ በሁለት ተከፈለ፤ የሕዝቡም እኩሌታ የጎናትን ልጅ ታምኒን ያነግሡት ዘንድ ተከተለው፤ እኩሌታውም ዘንበሪን ተከተለ።
22ዘንበሪንም የተከተለ ሕዝብ የጎናትን ልጅ ታምኒን በተከተለ ሕዝብ ላይ በረታ፤ ታምኒም ሞተ፥ ዘንበሪም ነገሠ።
23በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሠላሳ አንደኛው ዓመት ዘንበሪ በእስራኤል ላይ አሥራ ሁለት ዓመት ነገሠ። በቴርሳም ስድስት ዓመት ነገሠ።
24ከሳምርም በሁለት መክሊት ብር የሰማርያን ተራራ ገዛ፤ በተራራውም ላይ ሠራ፥ የሠራውንም ከተማ በተራራው ባለቤት በሳምር ስም ሰማርያ ብሎ ጠራው።
25ዘንበሪም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፥ ከእርሱም አስቀድሞ ከነበሩት ይልቅ እጅግ ከፋ።
26በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሁሉ በምናምንቴም ነገራቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ እስራኤልን ባሳተበት ኃጢአት ሄደ።
27የቀረውም ዘንበሪ ያደረገው ነገር፥ የሠራውም ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
28ዘንበሪም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ተቀበረ፤ ልጁም አክዓብ በፋንታው ነገሠ።
29በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዘንበሪ ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ የዘንበሪም ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ በሰማሪያ ሀያ ሁለት ዓመት ነገሠ።
30የዘንበሪም ልጅ አክዓብ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
31በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት መሄድ ታናሽ ነገር መሰለው፥ የሲዶናውያንንም ንጉሥ የኤትበኣልን ልጅ ኤልዛቤልን አገባ፥ ሄዶም በኣልን አመለከ ሰገደለትም።
32በሰማርያም በሠራው በበኣል ቤት ውስጥ ለበኣል መሠዊያ አቆመ።
33አክዓብም የማምለኪያ ዐፀድ ተከለ፤ አክዓብም ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያስቈጣውን ነገር አበዛ።
34በእርሱም ዘመን የቤቴል ሰው አኪኤል ኢያሪኮን ሠራ፤ በነዌም ልጅ በኢያሱ እጅ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ በበኵር ልጅ በአቢሮን መሠረትዋን አደረገ፥ በታናሹ ልጁም በሠጉብ በሮችዋን አቆመ። a