English

ምዕራፍ 8

1ኤልሳዕም ልጅዋን ያስነሣላትን ሴት። አንቺ ከቤተ ሰብሽ ጋር ተነሥተሽ ሂጂ፥ በምታገኚውም ስፍራ ተቀመጪ፤ እግዚአብሔር ራብ ጠርቶአል፤ ሰባት ዓመትም በምድር ላይ ይመጣል ብሎ ተናገራት።
2ሴቲቱም ተነሥታ እንደ እግዚአብሔር ሰው ቃል አደረገች፤ ከቤተ ሰብዋም ጋር ሄዳ በፍልስጥኤም አገር ሰባት ዓመት ተቀመጠች።
3ሰባቱም ዓመት በተፈጸመ ጊዜ ሴቲቱ ከፍልስጥኤም አገር ተመለሰች፤ ስለ ቤትዋና ስለ መሬትዋ ልትጮኽ ወደ ንጉሡ ወጣች።
4ንጉሡም ከእግዚአብሔር ሰው ሎሌ ከግያዝ ጋር። ኤልሳዕ ያደረገውን ተአምራት ሁሉ ንገረኝ እያለ ይጫወት ነበር።
5እርሱም የሞተውን እንደ አስነሣ ለንጉሡ ሲናገር፥ እነሆ፥ ልጅዋን ያስነሣላት ሴት ስለ ቤትዋና ስለ መሬትዋ ወደ ንጉሥ ጮኸች፤ ግያዝም። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ሴቲቱ ይህች ናት፥ ኤልሳዕም ያስነሣው ልጅዋ ይህ ነው አለ።
6ንጉሡም ሴቲቱን ጠየቀ፥ ነገረችውም። ንጉሡም። የነበረላትን ሁሉ፥ መሬትዋንም ከተወች ጀምራ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን የእርሻዋን ፍሬ ሁሉ መልስላት ብሎ ስለ እርስዋ ጃንደረባውን አዘዘ።
7ኤልሳዕም ወደ ደማስቆ መጣ፤ የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር ታምሞ ነበር፤ ወሬኞችም። የእግዚአብሔር ሰው ወደዚህ መጥቶአል ብለው ነገሩት።
8ንጉሡም አዛሄልን። ገጸ በረከት በእጅህ ወስደህ የእግዚአብሔርን ሰው ልትገናኝ ሂድ፤ በእርሱም አፍ። ከዚህ በሽታ እድናለሁን? ብለህ እግዚአብሔርን ጠይቅ አለው።
9አዛሄልም ሊገናኘው ሄደ፥ ከእርሱም ጋር ከደማስቆ መልካሙን ነገር ሁሉ የአርባ ግመል ጭነት ገጸ በረከት ወሰደ፤ መጥቶም በፊቱ ቆመና። ልጅህ የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር። ከዚህ በሽታ እድናለሁን? ሲል ወደ አንተ ልኮኛል አለ።
10ኤልሳዕም። ሂድ፥ መዳንስ ትድናለህ በለው፤ ነገር ግን እንዲሞት እግዚአብሔር አሳይቶኛል አለው።
11እስኪያፍርም ድረስ ትኵር ብሎ ተመለከተው፤ የእግዚአብሔርም ሰው አነባ።
12አዛሄልም። ጌታዬ ለምን ያነባል? አለ። እርሱም። በእስራኤል ልጆች ላይ የምታደርገውን ክፋት ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፥ ጕልማሶቻቸውንም በሰይፍ ትገድላለህ፥ ሕፃናቶቻቸውንም ትፈጠፍጣለህ፥ እርጉዞቻቸውንም ትቀድዳለህ አለው።
13አዛሄልም። ይህን ታላቅ ነገር አደርግ ዘንድ እኔ ውሻ ባሪያህ ምንድር ነኝ? አለ። ኤልሳዕም። አንተ በሶርያ ላይ ንጉሥ እንድትሆን እግዚአብሔር አሳይቶኛል አለው።
14ከኤልሳዕም ርቆ ወደ ጌታው መጣ፤ እርሱም። ኤልሳዕ ምን አለህ? አለው።
15እርሱም። እንድትፈወስ ነገረኝ አለው። በነጋውም ለሐፍ ወስዶ በውኃ ነከረው በፊቱም ላይ ሸፈነው፥ ሞተም። አዛሄልም በፋንታው ነገሠ።
16በእስራኤልም ንጉሥ በአክዓብ ልጅ በኢዮራም በአምስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም ነገሠ።
17መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ።
18የአክዓብንም ልጅ አግብቶ ነበርና የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ።
19ነገር ግን ለእርሱና ለልጆቹ ለዘመኑ ሁሉ መብራት ይሰጠው ዘንድ ተስፋ እንደ ሰጠ፥ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት እግዚአብሔር ይሁዳን ያጠፋ ዘንድ አልወደደም።
20በእርሱም ዘመን ኤዶምያስ ለይሁዳ እንዳይገብር ሸፈተ፥ በላያቸውም ንጉሥ አነገሡ።
21ኢዮራምም ከሰረገሎቹ ሁሉ ጋር ወደ ጸዒር አለፈ፤ በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሰረገሎቹን አለቆች ከብበው የነበሩትን የኤዶምያስን ሰዎች መታ፤ ሕዝቡ ግን ወደ ድንኳኑ ሸሸ።
22ኤዶምያስ ግን ለይሁዳ እንዳይገብር እስከ ዛሬ ድረስ ሸፈተ። በዚያም ዘመን ደግሞ ልብና ሸፈተ።
23የተረፈውም የኢዮራም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?
24ኢዮራምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በፋንታውም ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
25በእስራኤል ንጉሥ በአክዓብ ልጅ በኢዮራም በአሥራ ሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ።
26መንገሥ በጀመረ ጊዜ አካዝያስ የሀያ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ። እናቱም ጎቶልያ የተባለች የእስራኤል ንጉሥ የዘንበሪ ልጅ ነበረች።
27በአክዓብም ቤት መንገድ ሄደ፥ እንደ አክዓብም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ ለአክዓብ ቤት አማች ነበረና።
28ከአክዓብም ልጅ ከኢዮራም ጋር የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን በሬማት ዘገለዓድ ሊጋጠም ሄደ፤ ሶርያውንም ኢዮራምን አቆሰሉት።
29ንጉሡም ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን በሬማት ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ። የአክዓብም ልጅ ኢዮራም ታምሞ ነበርና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ሊያየው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።