English

ምዕራፍ 1

1በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አድርጎ እንዲህ አለ።
2የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል። የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤
3ከሕዝቡ ሁሉ በእንናተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፥ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ፤
4በሚኖርበትም ስፍራ ሁሉ ለቀረው ሰው የአገሩ ሰዎች በብርና በወርቅ በዕቃም በእንስሳም ይርዱት፤ ይህም በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ከሚያቀርቡት ሌላ ይሁን።
5የይሁዳና የብንያም የአባቶች ቤቶች አለቆችም፥ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ይወጡ ዘንድ እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው ሁሉ ተነሡ።
6በዙሪያቸውም ያሉ ሁሉ በፈቃዳቸው ካቀረቡት ሁሉ ሌላ በብር ዕቃና በወርቅ በገንዘቦችና በእንስሶች በሌላም ስጦታ አገዙአቸው።
7ንጉሡ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች አወጣ።
8የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም በመዝገቡ ላይ በነበረው በሚትሪዳጡ እጅ አወጣቸው፥ ለይሁዳም መስፍን ለሰሳብሳር ቈጠራቸው።
9ቍጥራቸውም ይህ ነው፤ ሠላሳ የወርቅ አንድ ሺህም የብር ሰሐኖች፥ ሀያ ዘጠኝም ቢላዎች፥
10ሠላሳ የወርቅ ደካዎች፥ አራት መቶ አሥርም ሌላ ዓይነት የብር ደካዎች፥ አንድ ሺህም ሌላ ዕቃ ነበረ።
11የወርቁና የብሩ ዕቃዎች ሁሉ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ፤ እነዚህንም ሁሉ ሰሳብሳር ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ ምርኮኞቹ ጋር ወሰደ።