ምዕራፍ 11
1እስራኤልም ሁሉ በኬብሮን ወደ ዳዊት ተሰብስበው። እነሆ፥ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቍራጭ ነን፤
2አስቀድሞ ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፤ አምላክህ እግዚአብሔርም። ሕዝቤን እስራኤልን አንተ ትጠብቃለህ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆናለህ 5ብሎህ ነበር አሉት።
3የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ በሳሙኤልም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል በእስራኤል ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊትን ቀቡት።
4ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ ኢያቡስ ወደምትባል ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፤ በአገሩም የተቀመጡ ኢያቡሳውያን በዚያ ነበሩ።
5በኢያቡስም የተቀመጡ ዳዊትን። ወደዚህ አትገባም አሉት፤ ዳዊት ግን አምባይቱን ጽዮንን ያዘ፤ እርሷም የዳዊት ከተማ ናት።
6ዳዊትም። ኢያቡሳውያንን አስቀድሞ የሚመታ ሰው አለቃና መኰንን ይሆናል አለ። የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ አስቀድሞ ወጣ፥ አለቃም ሆነ።
7ዳዊትም በአምባይቱ ውስጥ ተቀመጠ፤ ስለዚህም የዳዊት ከተማ ብለው ጠሩአት።
8ከሚሎም ጀምሮ በዙሪያው ከተማ ሠራ፤ ኢዮአብም የቀረውን ከተማ አበጀ።
9ዳዊትም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና እየበረታ ሄደ።
10ለዳዊትም የነበሩት የኃያላን አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ስለ እስራኤል እንደ ተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ያነግሡት ዘንድ ከእስራኤል ሁሉ ጋር በመንግሥቱ ላይ አጸኑት።
11የዳዊትም ኃያላን ቍጥር ይህ ነበረ፤ የሠላሳው አለቃ የአክሞናዊው ልጅ ያሾብአም ነበረ፤ እርሱ ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰው በአንድ ጊዜ ገደለ።
12ከእርሱም በኋላ በሦስቱ ኃያላን መካከል የነበረ የአሆሃሂው የዱዲ ልጅ አልዓዛር ነበር።
13እርሱ ከዳዊት ጋር በፈስደሚም ነበረ፥ በዚያም ገብስ በሞላበት እርሻ ውስጥ ፍልስጥኤማውያን ለሰልፍ ተሰብስበው ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ።
14በእርሻውም መካከል ቆመው ጠበቁት፥ ፍልስጥኤማውያንንም ገደሉ፤ እግዚአብሔርም በታላቅ ማዳን አዳናቸው።
15ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓለቱ ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር።
16በዚያም ጊዜ ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፥ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በቤተ ልሔም ነበረ።
17ዳዊትም። በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ማን ይሰጠኛል? ብሎ ተመኘ።
18እነዚህም ሦስቱ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ቀድደው ሄዱ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ቀዱ፤ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፥ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፍስሶ።
19ይህን አደርግ ዘንድ አምላኬ ይከልክለኝ፤ በነፍሳቸው የደፈሩትም እነዚህ ሰዎች ደም እጠጣለሁን? በነፍሳቸው አምጥተውታል አለ። ስለዚህም ይጠጣ ዘንድ አልወደደም። ሦስቱም ኃያላን ያደረጉት ይህ ነው።
20የኢዮአብም ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበረ፤ ጦሩንም በሦስት መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፥ በሦስቱም መካከል ስሙ የተጠራ ነበረ።
21በሁለተኛውም ተራ በሆኑት በሦስቱ መካከል የከበረ ነበረ፥ አለቃቸውም ሆነ፤ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም።
22በቀብስኤልም የነበረው፥ ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊን የአሪኤል ሁለቱን ልጆች ገደለ፤ በአመዳይም ወራት ወርዶ በጕድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ።
23ቁመቱም አምስት ክንድ የነበረውን ረጅሙን ግብጻዊውን ሰው ገደለ፤ በግብጻዊውም እጅ የሸማኔ መጠቅለያ የመሰለ ጦር ነበረ፤ እርሱ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፥ ከግብጻዊውም እጅ ጦሩን ነቅሎ በገዛ ጦሩ ገደለው።
24የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም በሦስቱ ኃያላን መካከል የተጠራ ነበር።
25እነሆ፥ ከሠላሳው ይልቅ የከበረ ነበረ፥ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በዘበኞቹ ላይ ሾመው።
26ደግሞም በጭፍሮች ዘንድ የነበሩት ኃያላን እነዚህ ናቸው፤ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ የቤተ ልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፥
27ሃሮራዊው ሳሞት፥ ፈሎናዊው ሴሌስ፥
28የቴቁሔ ሰው የዒስካ ልጅ ዒራስ፥
29ዓናቶታዊው አቢዔዜር፥ ኩሳታዊው ሴቤካይ፥
30አሆሃዊው ዔላይ፥ ነጦፋዊው ኖኤሬ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌድ፥
31ከብንያም ወገን ከግብዓ የሪባይ ልጅ ኤታይ፥
32ጲርዓቶናዊው በናያስ፥ የገዓስ ወንዝ ሰው ኡሪ፥
33ዓረባዊው አቢኤል፥ ባሕሩማዊው ዓዝሞት፥
34ሰዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ የጊዞናዊው የአሳን ልጆች፥ የሃራራዊው የሻጌ ልጅ ዮናታን፥
35የአሮዳዊው የአራር ልጅ አምናን፥
36የኡር ልጅ ኤሊፋል፥ ሚኬራታዊው ኦፌር፥
37ፍሎናዊው አኪያ፥ ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፥ የኤዝባይ ልጅ ነዕራይ፥
38የናታንም ወንድም ኢዮኤል፥ የሐግሪ ልጅ ሚብሐር፥
39አሞናዊው ጼሌቅ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮታዊው ነሃራይ፥
40ይትራዊው ዒራስ፥ ይትራዊው ጋሬብ፥
41ኬጢያዊው ኦርዮ፥ የአሕላይ ልጅ ዛባድ፥
42የሮቤላዊው የሺዛ ልጅ ዓዲና፥ እርሱ የሮቤላውያን አለቃ ነበረ፥
43ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሰዎች ነበሩ፥ የማዕካ ልጅ ሐናን፥ ሚትናዊው ኢዮሣፍጥ፥
44አስታሮታዊው ዖዝያ፥ የአሮኤራዊው የኮታም ልጆች ሻማና ይዒኤል፥
45የሽምሪ ልጅ ይድኤል፥ ወንድሙም ይድኤል፥ ወንድሙም ቲዳዊው ዮሐ፥
46መሐዋዊው ኤሊኤል፥ ይሪባይ፥ ዮሻዊያ፥ የኤልናዓም ልጆች፥ ሞዓባዊው ይትማ፥
47ኤልኤል፥ ዖቤድ፥ ምጾባዊው የዕሢኤል።