ምዕራፍ 13
1ዳዊትም ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ከአለቆቹም ሁሉ ጋር ተማከረ።
2ዳዊትም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ። መልካም መስሎ የታያችሁ እንደሆነ፥ ከአምላካችን ከእግዚአብሔርም ወጥቶ እንደ ሆነ፥ በእስራኤል አገር ሁሉ ለቀሩት ወንድሞቻችን በከተሞቻቸውና በመሰምሪያዎቻቸውም ለሚቀመጡ ካህናትና ሌዋውያን ወደ እኛ ይሰበሰቡ ዘንድ እንላክ፤
3በሳኦልም ዘመን አልፈለግነውምና የአምላካችንን ታቦት ወደ እኛ እንመልስ አላቸው።
4ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዓይን ዘንድ ቅን ነበረና ጉባኤው ሁሉ። እንዲሁ እናደርጋለን አሉ።
5የእግዚአብሔርንም ታቦት ከቂርያትይዓሪም ያመጡ ዘንድ ዳዊት እስራኤልን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ከሺሖር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ሰበሰበ።
6ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ በኪሩቤል ላይ የተቀመጠውን ስሙም በእርሱ የተጠራውን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያወጡ ዘንድ በይሁዳ ወዳለችው ቂርያትይዓሪም ወደ ተባለች ወደ በኣላ ሄዱ።
7የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑት፥ ከአሚናዳብም ቤት አመጡት፤ ዖዛና አሒዮም ሠረገላውን ይነዱ ነበር።
8ዳዊትና እስራኤል ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆና በከበሮ በጸናጽልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር።
9ወደ ኪዶንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ታቦቱን ሊይዝ ዖዛ እጁን ዘረጋ።
10የእግዚአብሔርም ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እጁንም ወደ ታቦቱ ስለ ዘረጋ ቀሠፈው፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ።
11እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ቀሠፈው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያን ስፍራ ስም የዖዛ ስብራት ብሎ ጠራው።
12በዚያም ቀን ዳዊት። የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት አመጣለሁ ብሎ እግዚአብሔርን ፈራ።
13ዳዊትም ታቦቱን ወደ ጌት ሰው ወደ አቢዳራ ቤት አሳለፈው እንጂ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ አላመጣውም።
14የእግዚአብሔርም ታቦት በአቢዳራ ቤተሰብ ዘንድ በቤቱ ውስጥ ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም የአቢዳራን ቤትና ያለውን ሁሉ ባረከ።