English

ምዕራፍ 23

1ዳዊትም በሸመገለ ጊዜ፥ ዕድሜንም በጠገበ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን በእስራኤል ላይ አነገሠው።
2የእስራኤልንም አለቆች ሁሉ፥ ካህናቱንም፥ ሌዋውያኑንም ሰበሰበ።
3ሌዋውያንም ከሠላሳ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ ተቈጠሩ፤ ቍጥራቸው በእያንዳንዱ ነፍስ ወከፍ ሠላሳ ስምንት ሺህ ነበረ።
4ከእነዚህም ውስጥ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ የሚያሠሩት ሀያ አራት ሺህ ነበሩ፤ ስድስቱ ሺህም አለቆችና ፈራጆች ነበሩ።
5አራቱ ሺህም በረኞች ነበሩ፤ አራቱ ሺህም ለምስጋና በተሠሩት በዜማ ዕቃዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።
6ዳዊትም እንደ ሌዊ ልጆች እንደ ጌድሶንና እንደ ቀዓት እነደ ሜራሪም በየሰሞናቸው ከፈላቸው።
7ከጌድሶናውያን ለአዳንና ሰሜኢ ነበሩ።
8የለአዳን ልጆች አለቃው ይሒኤል፥ ዜቶም፥ ኢዮኤል ሦስት ነበሩ።
9የሰሜኢ ልጆች ሰሎሚት፥ ሐዝኤል፥ ሐራን ሦስት ነበሩ። እነዚህ የለአዳን አባቶች ቤቶች አለቆች ነበሩ።
10የሰሜኢ ልጆች ኢኢት፥ ዚዛ፥ የዑስ፥ በሪዓ ነበሩ። እነዚህ አራቱ የሰሜኢ ልጆች ነበሩ።
11አለቃው ኢኢት ነበረ፤ ሁለተኛው ዚዛ ነበረ፤ የዑስና በሪዓ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህ እንደ አንድ አባት ቤት ሆነው ተቈጠሩ።
12የቀአት ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል አራት ነበሩ።
13የእንበረም ልጆች አሮንና ሙሴ ነበሩ፤ አሮንም ከሁሉ በላይ የተቀደሰ ይሆን ዘንድ ተለየ፥ እርሱና ልጆቹ፥ ለዘላለም በእግዚአብሔር ፊት ያጥንና ያገለግል ዘንድ፥ በስሙም ለዘላለም ይባርክ ዘንድ።
14የእግዚአብሔርም ሰው የሙሴ ልጆች በሌዊ ነገድ ተቈጠሩ።
15የሙሴ ልጆች ጌርሳምና አልዓዛር ነበሩ።
16የጌርሳም ልጆች አለቃ ሱባኤል ነበረ።
17የአልዓዛርም ልጆች አለቃ ረዓብያ ነበረ፤ አልዓዛርም ሌሎች ልጆች አልነበሩትም፤ የረዓብያ ልጆች እጅግ ብዙ ነበሩ።
18የይስዓር ልጆች አለቃው ሰሎሚት ነበረ።
19የኬብሮን ልጆች አለቃው ይሪያ፥ ሁለተኛው አማርያ፥ ሦስተኛው የሕዚኤል፥ አራተኛው ይቅምዓም ነበሩ።
20የዑዝኤል ልጆች አለቃው ሚካ፥ ሁለተኛው ይሺያ ነበሩ።
21የሜራሪ ልጆች ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ። የሞሖሊ ልጆች አልዓዛርና ቂስ ነበሩ።
22አልዓዛርም ሴቶች ልጆች ብቻ እንጂ ወንዶች ልጆች ሳይወልድ ሞተ፤ ወንድሞቻቸውም የቂስ ልጆች አገቡአቸው።
23የሙሲ ልጆች ሞሖሊ፥ ዔደር፥ ኢያሪሙት ሦስት ነበሩ።
24የእግዚአብሔርን ቤት አገልግሎት በሠሩ ከሀያ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ በነበሩ በእያንዳንዳቸው በስማቸው በተቆጠሩት ላይ የአባቶች ቤት አለቆች የሆኑት በየአባቶቻቸው ቤት የሌዊ ልጆች እነዚህ ነበሩ።
25ዳዊትም። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዕረፍት ሰጥቶአል፥ በኢየሩሳሌምም ለዘላለም የቀመጣል።
26ሌዋውያንም ከእንግዲህ ወዲህ ማደሪያውንና የማገልገያውን ዕቃ ሁሉ አይሸከሙም አለ።
27በመጨረሻውም በዳዊት ትእዛዝ ከሀያ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት የሌዊ ልጆች ተቈጠሩ።
28ሥራቸውም የእግዚአብሔርን ቤት በየአደባባዩና በየጓዳው ውስጥ ለማገልገል፥ ቅዱሱንም ዕቃ ሁሉ ለማንጻት፥ የእግዚአብሔርንም ቤት አገልግሎት ለመሥራት ከአሮን ልጆች እጅ በታች ነበረ።
29ደግሞም ገጸ ኅብስት፥ ስስ ቂጣም ቢሆን፥ በምጣድም ቢጋገር፥ ቢለወስም፥ ለእህል ቍርባን በሆነው በመልካሙ ዱቄት በመስፈሪያና በልክ ሁሉ ያገለግሉ ነበር።
30ሥራቸውም በየጥዋቱና በየማታው ቆመው እግዚአብሔርን ለማመስገንና ለማክበር፥
31በየሰንበታቱም በየመባቻዎቹም በየበዓላቱም እንደ ሥርዓቱ ቍጥር በእግዚአብሔር ፊት ዘወትር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ ለማቅረብ፥
32ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የመገናኛውን ድንኳን ሥርዓት የመቅደሱንም ሥርዓት የወንድሞቻቸውንም የአሮንን ልጆች ሥርዓት ለመጠበቅ ነበረ።