English

ምዕራፍ 27

1የእስራኤልም ልጆች የአባቶች ቤቶች አለቆችና የሺህ አለቆች የመቶ አለቆችም በክፍሎች ነገር ሁሉ ንጉሡን ያገለገሉትም ሹማምት እንደ ቍጥራቸው እነዚህ ነበሩ። እነዚህም ክፍሎች እያንዳንዳቸው ሀያ አራት ሺህ ሆነው በዓመት ወራት ሁሉ በየወሩ ይገቡና ይወጡ ነበር።
2ለመጀመሪያው ወር በአንደኛው ክፍል ላይ የዘብድኤል ልጅ ያሾብዓም ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ።
3እርሱ ከፋሬስ ልጆች ነበረ፤ ለመጀመሪያው ወር በጭፍራ አለቆች ሁሉ ላይ ተሾሞ ነበር።
4በሁለተኛውም ወር ክፍል ላይ አሆሃዊው ዱዲ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ።
5ለሦስተኛው ወር ሦስተኛው የጭፍራ አለቃ የካህኑ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ።
6ይህ በናያስ በሠላሳው መካከል ኃያል ሆኖ በሠላሳው ላይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ልጁ ዓሚዛባድ ነበረ።
7ለአራተኛው ወር አራተኛው አለቃ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ ከእርሱም በኋላ ልጁ ዝባድያ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበር።
8ለአምስተኛው ወር አምስተኛው አለቃ ይዝራዊው ሸምሁት ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ።
9ለስድስተኛው ወር ስድስተኛው አለቃ የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ።
10ለሰባተኛው ወር ሰባተኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የሆነ ፍሎናዊው ሴሌስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ።
11ለስምንተኛው ወር ስምንተኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ኩሳታዊው ሲቦካይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ።
12ለዘጠኝኛው ወር ዘጠኝኛው አለቃ ከብንያማውያን የነበረው ዓናቶታዊው አቢዔዜር ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ።
13ለአሥረኛው ወር አሥረኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ነጦፋዊው ኖኤሬ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ።
14ለአሥራ አንደኛው ወር አሥራ አንደኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የነበረው ጲርዓቶናዊው በናያስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ።
15ለአሥራ ሁለተኛው ወር አሥራ ሁለተኛው አለቃ ከጎቶንያል ወገን የነበረው ነጦፋዊው ሔልዳይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሀያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ።
16በእስራኤልም ነገዶች ላይ እነዚህ ነበሩ በሮቤላውያን ላይ የዝክሪ ልጅ አልዓዛር አለቃ ነበረ፤ በስምዖናውያን የመዓካ ልጅ ሰፋጥያስ፤
17በሌዊ ላይ የቀሙኤል ልጅ ሐሸቢያ፤
18በአሮን ላይ ሳዶቅ፤ በይሁዳ ላይ ከዳዊት ወንድሞች ኤሊሁ፤ በይሳኮር ላይ የሚካኤል ልጅ ዖምሪ፤
19በዛብሎን ላይ የአብድዩ ልጅ ይሽማያ፤ በንፍታሌም ላይ የዓዝሪኤል ልጅ ኢያሪሙት፤
20በኤፍሬም ልጆች ላይ የዓዛዝያ ልጅ ሆሴዕ፤ በምናሴ ነገድ እኵሌታ ላይ የፈዳያ ልጅ ኢዩኤል፤
21በገለዓድ ባለው በምናሴ ነገድ እኵሌታ ላይ የዘካርያስ ልጅ አዶ፤ በብንያም ላይ የአበኔር ልጅ የዕሢኤል፤
22በዳን ላይ የይሮሐም ልጅ ዓዛርኤል፤ እነዚህ የእስራኤል ልጆች ነገዶች አለቆች ነበሩ።
23እግዚአብሔር ግን እስራኤልን እንደ ሰማይ ከዋክብት ያበዛ ዘንድ ተናግሮ ነበርና ዳዊት ከሀያ ዓመት በታች የነበሩትን አልቈጠረም።
24የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ መቍጠር ጀመረ፥ ነገር ግን አልፈጸመም፤ ስለዚህም በእስራኤል ላይ ቍጣ ሆነ፥ ቍጥራቸውም በንጉሡ በዳዊት መዝገብ አልተጻፈም።
25በንጉሡም ቤተ መዛግብት ላይ የዓዲኤል ልጅ ዓዝሞት ሹም ነበረ፤ በሜዳውም በከተሞችም በመንደሮችም በግንቦችም ቤተ መዛግብት ላይ የዖዝያ ልጅ ዮናታን ሹም ነበረ፤
26መሬቱን የሚያበጃጁትና እርሻውን በሚያርሱት ላይ የክሉብ ልጅ ዔዝሪ ሹም ነበረ፤
27በወይንም ቦታዎች ላይ ራማታዊው ሰሜኢ ሹም ነበረ፤ ለወይንም ጠጅ ዕቃ ቤት በሚሆነው በወይኑ ሰብል ላይ ሸፋማዊው ዘብዲ ሹም ነበረ፤
28በቈላውም ውስጥ ባሉት በወይራውና በሾላው ዛፎች ላይ ጌድራዊው በአልሐናን ሹም ነበረ፤ በዘይቱም ቤቶች ላይ ኢዮአስ ሹም ነበረ፤
29በሳሮንም በሚሰማሩ ከብቶች ላይ ሳሮናዊው ሰጥራይ ሹም ነበረ፤ በሸለቆቹም ውስጥ በነበሩት ከብቶች ላይ የዓድላይ ልጅ ሻፍጥ ሹም ነበረ፤
30በግመሎችም ላይ እስማኤላዊው ኡቢያስ ሹም ነበረ፤ በአህዮቹም ላይ ሜሮኖታዊው ይሕድያ ሹም ነበረ፤
31በመንጎቹም ላይ አጋራዊው ያዚዝ ሹም ነበረ። እነዚህ ሁሉ በንጉሡ በዳዊት ሀብት ላይ ሹሞች ነበሩ።
32አስተዋይና ጸሐፊ የነበረው የዳዊት አጎት ዮናታን አማካሪ ነበረ፤ የሐክሞኒም ልጅ ይሒኤል ከንጉሡ ልጆች ጋር ነበረ፤
33አኪጦፌልም የንጉሡ አማካሪ ነበረ፤ አርካዊውም ኩሲ የንጉሡ ወዳጅ ነበረ፤
34ከአኪጦፌልም ቀጥሎ የበናያስ ልጅ ዮዳሄና አብያታር ነበሩ፤ ኢዮአብም የንጉሡ ሠራዊት አለቃ ነበረ።