ምዕራፍ 5
1የእስራኤልም በኵር የሮቤል ልጆች እነዚህ ናቸው። እርሱ የበኵር ልጅ ነበረ፤ ነገር ግን የአባቱን ምንጣፍ ስላረከሰ ብኵርናው ለእስራኤል ልጅ ለዮሴፍ ልጆች ተሰጠ፤ ትውልዱ ግን ከብኵርና ጋር አልተቈጠረም።
2ይሁዳም በወንድሞቹ መካከል በረታ፥ አለቃም ከእርሱ ሆነ፤ ብኵርናው ግን ለዮሴፍ ነበረ።
3የእስራኤል በኵር የሮቤል ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ከርሚ ነበሩ።
4የኢዮኤል ልጆች፤ ልጁ ሸማያ፥
5ልጁ ጎግ፥ ልጁ ሰሜኢ፥ ልጁ ሚካ፥
6ልጁ ራያ፥ ልጁ ቢኤል፥ የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር የማረከው ልጁ ብኤራ፤ እርሱ የሮቤል ነገድ አለቃ ነበረ።
7ወንድሞቹ በየወገናቸው የትውልዶቻቸው መዝገብ በተቈጠረ ጊዜ፤ አንደኛው ኢዮኤል፥
8ዘካርያስ፥ እስከ ናባውና እስከ በኣልሜዎን ድረስ በአሮዔር የተቀመጠው የኢዮኤል ልጅ የሽማዕ ልጅ የዖዛዝ ልጅ ቤላ፤
9በገለዓድ ምድር እንስሶቻቸው በዝተው ነበርና በምሥራቅ በኩል ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምድረ በዳው መግቢያ ድረስ ተቀመጠ።
10በሳኦልም ዘመን ከአጋራውያን ጋር ተዋጉ፥ እነርሱም በእጃቸው ተመትተው ወደቁ፤ በገለዓድ ምሥራቅ በኩል ባለው አገር ሁሉ በድንኳኖቻቸው ተቀመጡ።
11የጋድም ልጆች በባሳን ምድር እስከ ሰልካ ድረስ በአፋዛዣቸው ተቀመጡ።
12አንደኛው ኢዮኤል፥ ሁለተኛው ሳፋም፥ ያናይ፥ ሳፋጥ በበሳን ተቀመጡ።
13የአባቶቻቸውም ቤቶች ወንድሞች ሚካኤል፥ ሜሱላም፥ ሳባ፥ ዮራይ፥ ያካን፥ ዙኤ፥ ኦቤድ ሰባት ነበሩ።
14እነዚህም የቡዝ ልጅ የዬዳይ ልጅ የኢዬሳይ ልጅ የሚካኤል ልጅ የገለዓድ ልጅ የኢዳይ ልጅ የዑሪ ልጅ የአቢካኢል ልጆች ነበሩ።
15የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቃ የጉኒ ልጅ የአብዲኤል ልጅ ወንድም ነበረ።
16በገለዓድም ምድር በባሳን በመንደሮቹም በሳሮንም መሰምርያዎች ሁሉ እስከ ዳርቻቸው ድረስ ተቀምጠው ነበር።
17እነዚህ ሁሉ በትውልዶቻቸው በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአታም ዘመንና በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም ዘመን ተቈጠሩ።
18የሮቤልና የጋድ ልጆች የምናሴም ነገድ እኵሌታ፥ ጽኑዓን፥ ጋሻና ሰይፍ የሚይዙ፥ ቀስተኞችም፥ ሰልፍ የሚያውቁ ሰልፈኞችም፥ አርባ አራት ሺህ ሰባት መቶ ስድሳ ነበሩ።
19ከአጋራውያንና ከኢጡር ከናፌስና ከናዳብ ጋር ተዋጉ።
20በሚዋጉበትም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኸዋልና፥ በእርሱም ታምነዋልና ተለመናቸው፤ በላያቸውም ረዳት ሆናቸው፥ አጋራውያንና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም ሁሉ በእጃቸው ተሰጡ።
21ከከብቶቻቸውም አምሳ ሺህ ግመሎች፥ ሁለት መቶ አምሳ ሺህም በጎች፥ ሁለት ሺህም አህዮች፥ ከሰዎችም መቶ ሺህ ማረኩ።
22ሰልፉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበረና ብዙ ሰዎች ተገድለው ወደቁ፤ እስከ ምርኮም ዘመን ድረስ በስፍራቸው ተቀመጡ።
23የምናሴ የነገድ እኵሌታ ልጆች በምድሪቱ ተቀመጡ። ከባሳንም ጀምሮ እስከ በኣልአርሞንዔምና እስከ ሳኔር እስከ አርሞንዔም ተራራ ድረስ በዙ።
24የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች እነዚህ ነበሩ፤ ዔፌር፥ ይሽዒ፥ ኤሊኤል፥ ዓዝርኤል፥ ኤርምያ፥ ሆዳይዋ፥ ኢየድኤል፤ እነርሱ ጽኑዓን ኃያላን የታወቁ ሰዎች የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች ነበሩ።
25የአባቶቻቸውንም አምላክ በደሉ፥ እግዚአብሔርም ከፊታቸው ባጠፋቸው በምድሩ አሕዛብ አማልክት አመነዘሩ።
26የእስራኤልም አምላክ የአሦርን ንጉሥ የፎሐን መንፈስ፥ የአሦርንም ንጉሥ የቴልጌልቴልፌልሶርን መንፈስ አስነሣ፤ የሮቤልንና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኵሌታ አፈለሰ፥ እስከ ዛሬም ወዳሉበት ወደ አላሔና ወደ ኦቦር፥ ወደ ሃራና ወደ ጎዛን ወንዝ አመጣቸው።