English

ምዕራፍ 14

1አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አሳ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። በእርሱም ዘመን ምድሪቱ አሥር ዓመት ያህል ዐረፈች።
2አሳም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን ነገር አደረገ፤
3የእንግዶቹንም አማልክት መሠዊያ የኮረብታውንም መስገጃዎች አፈረሰ፥ ሐውልቶቹንም ሰበረ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤
4የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ፥ ሕጉንና ትእዛዙንም ያደርጉ ዘንድ ይሁዳን አዘዘ።
5ከይሁዳም ከተሞች ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችና የፀሐይ ምስሎችን አስወገደ፤ መንግሥቱም በእርሱ ሥር በሰላም ተቀመጠች።
6በይሁዳም ምሽጎች ከተሞችን ሠራ፤ እግዚአብሔርም ዕረፍት ስለ ሰጠው ምድሪቱ ጸጥ ብላ ነበር፥ በዚያም ዘመን ሰልፍ አልነበረም።
7ይሁዳንም። እነዚህን ከተሞች እንሥራ፥ ቅጥርም ግንብም መዝጊያም መወርወሪያም እናድርግባቸው፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን ስለ ፈለግነው ምድሪቱ ገና በፊታችን ናት፤ እኛ ፈልገነዋል፥ እርሱም በዙሪያችን ዕረፍት ሰጥቶናል አለ። እነርሱም ሠሩ አከናወኑም።
8ለአሳም አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦር የሚሸከሙ ሦስት መቶ ሺህ የይሁዳ ሠራዊት፥ ጋሻም የሚሸከሙ ቀስትም የሚገትሩ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህም ሁሉ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ።
9ኢትዮጵያዊውም ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰዎችና ሦስት መቶ ሰረገሎች ይዞ ወጣባቸው፤ ወደ መሪሳም መጣ።
10አሳም ሊጋጠመው ወጣ፥ በመሪሳም አጠገብ ባለው በጽፋታ ሸለቆ ውስጥ ተሰለፉ።
11አሳም። አቤቱ፥ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ማዳን አይሳንህም፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ በአንተ ታምነናልና፥ በስምህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥተናልና እርዳን፤ አቤቱ፥ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህ ብሎ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
12እግዚአብሔርም በአሳና በይሁዳ ፊት ኢትዮጵያውያንን መታ፤ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ።
13አሳም ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ እስከ ጌራራ ድረስ አሳደዱአቸው፤ ኢትዮጵያውያንም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ወደቁ፥ በእግዚአብሔርና በሠራዊቱ ፊት ተሰባብረዋልና፤ እጅግም ብዙ ምርኮ ወሰዱ።
14ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ ስለ ወደቀባቸው በጌራራ ዙሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ መቱ፤ በከተሞቹም ውስጥ እጅግ ብዝበዛ ነበረና ከተሞቹን ሁሉ በዘበዙ።
15የከብቶቹንም በረት አፈረሱ፤ እጅግም ብዙ በጎችንና ግመሎችንም ማረኩ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ።