ምዕራፍ 20
1እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ በኋላ የሞዓብና የአሞን ልጆች ከእነርሱም ጋር ምዑናውያን ኢዮሣፍጥን ሊወጉ መጡ።
2ወሬኞችም መጥተው። ከባሕሩ ማዶ ከሶሪያ ታላቅ ሠራዊት መጥቶብሃል፤ እነሆም፥ ዓይንጋዲ በተባለች በሐሴሶን ታማር ናቸው ብለው ለኢዮሣፍጥ ነገሩት።
3ኢዮሣፍጥም ፈራ፥ እግዚአብሔርንም ሊፈልግ ፊቱን አቀና፤ በይሁዳም ሁሉ ጾም አወጀ።
4ይሁዳም እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ተከማቸ፤ ከይሁዳ ከተሞችም ሁሉ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ መጡ።
5ኢዮሣፍጥም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በአዲሱ አደባባይ ፊት ቆመ፤
6እንዲህም አለ። አቤቱ የአባቶቻችን አምላክ ሆይ፥ በሰማይ ያለህ አምላክ አንተ አይደለህምን? የአሕዛብንስ መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህምን? ኃይልና ችሎታ በእጅህ ነው፥ ሊቋቋምህም የሚችል የለም።
7አምላካችን ሆይ፥ በዚህ ምድር የነበሩትን አሕዛብ ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት ያሳደድህ፥ ለወዳጅህም ለአብርሃም ዘር ለዘላለም የሰጠሃት አንተ አይደለህምን?
8እነርሱም የተቀመጡባት፥ ለስምህም መቅደስን ሠርተውባት።
9ክፉ ነገር፥ የፍርድ ሰይፍ ወይም ቸነፈር ወይም ራብ፥ ቢመጣብን ስምህ ባለበት በዚህ ቤት ፊትና በፊትህ ቆመን በመከራችን ወደ አንተ እንጮኻለን፥ አንተም ሰምተህ ታድነናለህ አሉ።
10አሁንም፥ እነሆ፥ እስራኤል ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ ያልፉባቸው ዘንድ ያልፈቀድህላቸው፥ ነገር ግን ፈቀቅ ብለው ያላጠፉአቸው፥ የአሞንና የሞዓብ ልጆች የሴይርም ተራራ ሰዎች፥
11እነሆ፥ ለወሮታችን ክፋት ይመልሱልናል፤ ከሰጠኸንም ርስት ያወጡን ዘንድ መጥተዋል።
12አምላካችን ሆይ፥ አንተ አትፈርድባቸውምን? ይህን የመጣብንን ታላቅ ወገን እንቃወም ዘንድ አንችልም፤ የምናደርገውንም አናውቅም፤ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው።
13የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ከሕፃናቶቻቸውና ከሚስቶቻቸው ከልጆቻቸውም ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ነበር።
14የእግዚአብሔርም መንፈስ ከአሳፍ ወገን በነበረው በሌዋዊው በማታንያ ልጅ በይዒኤል ልጅ በበናያስ ልጅ በዘካሪያስ ልጅ በየሕዚኤል ላይ በጉባኤው መካከል መጣ፤
15እንዲህም አለ። ይሁዳ ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ፥ አንተም ንጉሡ ኢዮሣፍጥ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል። ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፥ አትደንግጡም።
16ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነሆ፥ በጺጽ ዓቀበት ይወጣሉ፤ በሸለቆውም መጨረሻ በይሩኤል ምድረ በዳ ፊት ለፊት ታገኙአቸዋላችሁ።
17እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ተሰለፉ፥ ዝም ብላችሁ ቁሙ፥ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፥ አትደንግጡም፥ ነገም ውጡባቸው።
18ኢዮሣፍጥም በምድር ላይ ተደፋ ይሁዳም ሁሉ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገዱ።
19ሌዋውያንም፥ የቀዓት ልጆችና የቆሬ ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በእጅግ ታላቅ ድምፅ ያመሰገኑት ዘንድ ቆሙ።
20ማልደውም ተነሡ፥ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና። ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሰላላችኋል አለ።
21ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን። ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉትንም፥ ጌጠኛ ልብስም ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔርም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ።
22ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተመቱ።
23የአሞንና የሞዓብ ልጆችም በሴይር ተራራ በሚኖሩት ላይ ፈጽመው ይገድሉአቸው ዘንድ ያጠፉአቸውም ዘንድ ተነሥተውባቸው ነበር፤ በሴይርም የሚኖሩትን ካጠፉ በኋላ እያንዳንዱ ባልንጀራውን ለማጥፋት ተረዳዳ።
24የይሁዳም ሰዎች ወደ ምድረ በዳ ግንብ በመጡ ጊዜ ሕዝቡን አዩ፤ እነሆም፥ በምድሩ ሁሉ ሬሳ ሞልቶ ነበር፥ ያመለጠም ሰው አልነበረም።
25ኢዮሣፍጥና ሕዝቡም ምርኮ ይወስዱ ዘንድ መጡ ብዙ ከብትና ልዩ ልዩ ዕቃም፥ ልብስም፥ እጅግም ያማረ ዕቃ አገኙ፥ በዘበዙትም፥ ሁሉንም ይሸከሙ ዘንድ አልቻሉም፤ ከምርኮውም ብዛት የተነሣ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ይበዘብዙ ነበር።
26በአራተኛውም ቀን በበረከት ሸለቆ ውስጥ ተሰበሰቡ፥ በዚያም እግዚአብሔርን ባረኩ፤ ስለዚህም ያ ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተባለ።
27የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች፥ በፊታቸውም ኢዮሣፍጥ፥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ ደስ አሰኝቶአቸዋልና በደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ዘንድ ተመለሱ።
28በበገናም በመሰንቆም በመለከትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገቡ።
29እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንደ ወጋ በሰሙ ጊዜ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ፍርሃት ሆነ።
30የኢዮሣፍጥም መንግሥት ጸጥ አለች፥ አምላኩም በዙሪያው ካሉ አሳረፈው።
31ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜም የሠላሳ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሀያ አምስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች።
32በአባቱም በአሳ መንገድ ሄደ፥ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔር ፊት ቅን አደረገ።
33ነገር ግን የኮረብታው መስገጃዎች አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና ልባቸውን ወደ አባቶቻቸው አምላክ አላዘጋጁም ነበር።
34የቀረውም የፊተኛውና የኋለኛው የኢዮሣፍጥ ነገር፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው በአናኒ ልጅ በኢዩ ታሪክ ተጽፎአል።
35ከዚህም በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሥራው እጅግ ክፉ ከሆነ ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር ተባበረ።
36ወደ ተርሴስም የሚሄዱትን መርከቦች ያሠሩ ዘንድ አንድ ሆኑ፤ መርከቦቹንም በዔጽዮንጋብር አሠሩ።
37የመሪሳም ሰው የዶዳያ ልጅ አልዓዛር። ከአካዝያስ ጋር ተባብረሃልና እግዚአብሔር ሥራህን አፍርሶታል ብሎ በኢዮሣፍጥ ላይ ትንቢት ተናገረ። መርከቦቹም ተሰበሩ፥ ወደ ተርሴስም ይሄዱ ዘንድ አልቻሉም።