ምዕራፍ 31
1ይህም ሁሉ በተፈጸመ ጊዜ በዚያ የተገኙ እስራኤል ሁሉ ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው ሁሉን ፈጽመው እስካጠፉአቸው ድረስ ሐውልቶቹን ሰባበሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጡ፥ በይሁዳና በብንያምም ሁሉ ደግሞም በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኮረብታው መስገጃዎችና መሠዊያዎች አፈረሱ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወደ ርስታቸውና ወደ ከተሞቻቸው ተመለሱ።
2ሕዝቅያስም የካህናትንና የሌዋውያንን ሰሞን በየክፍላቸውና በየአገልግሎታቸው አቆመ፤ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ በሮች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ያገለግሉም ዘንድ፥ ያመሰግኑም ያከብሩም ዘንድ ካህናቱንና ሌዋውያኑን አቆመ።
3በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ተጻፈ በጥዋትና በማታ፥ በሰንበታቱም፥ በመባቻዎቹም፥ በበዓላትም ለሚቀርበው ለሚቃጠለው መሥዋዕት ንጉሡ ከገንዘቡ የሚከፍለውን ወሰነ።
4በእግዚአብሔርም ቤት ለአገልግሎት እንዲጸኑ ለካህናቱና ለሌዋውያን ክፍላቸውን ይሰጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሕዝብ አዘዘ።
5ይህንም ነገር እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች የእህሉንና የወይኑን ጠጅ የዘይቱንና የማሩንም፥ የእርሻውንም ፍሬ ሁሉ በኵራት ሰጡ፤ የሁሉንም አሥራት አብዝተው አቀረቡ።
6በይሁዳም ከተሞች የሚኖሩ የእስራኤልና የይሁዳ ልጆች የበሬውንና የበጉን አሥራት፥ ለአምላካቸውም ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን አሥራት አመጡ፥ ከምረውም አኖሩት።
7በሦስተኛው ወር መከመር ጀመሩ፤ በሰባተኛውም ወር ጨረሱ።
8ሕዝቅያስና አለቆቹም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርና ሕዝቡን እስራኤልን ባረኩ።
9ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቀ።
10ከሳዶቅም ወገን የሆነ ዋነኛው ካህን ዓዛሪያስ። ሕዝቡ ቍርባኑን ወደ እግዚአብሔር ቤት ማቅረብ ከጀመረ ወዲህ በልተናል፥ ጠግበናልም፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ባርኮአልና ብዙ ተርፎአል፤ የተረፈውም ይህ ክምር ትልቅ ነው ብሎ ተናገረ።
11ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤት ጐተራ ያዘጋጁ ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም አዘጋጁ።
12ቍርባኑና አሥራቱን የተቀደሱትንም በእምነት ወደዚያ አገቡት። ሌዋዊውም ኮናንያ ተሾመባቸው፥ ወንድሙም ሰሜኢ በማዕርግ ሁለተኛ ነበረ፤
13በንጉሡም በሕዝቅያስና በእግዚአብሔር ቤት አለቃ በዓዛርያስ ትእዛዝ ይሒዒል፥ ዓዛዝያ፥ ናሖት፥ አሣሄል፥ ይሬሞት፥ ዮዛባት፥ ኤሊኤል፥ ሰማኪያ፥ መሐት፥ በናያስ፥ ከኮናንያና ከወንድሙ ከሰሜኢ እጅ በታች ተቈጣጣሪዎች ነበሩ።
14የሌዋዊውም የይምና ልጅ የምሥራቁ ደጅ በረኛ ቆሬ የእግዚአብሔርን መባና የተቀደሱትን ነገሮች እንዲያካፍል ሕዝቡ ለእግዚአብሔር በፈቃድ ባቀረቡት ላይ ተሾመ።
15በካህናቱም ከተሞች ለታላላቆችና ለታናናሾች ወንድሞቻቸው በየሰሞናቸው ክፍላቸውን በእምነት ይሰጡ ዘንድ ዔድን፥ ሚንያሚን፥ ኢያሱ፥ ሸማያ፥ አማርያ፥ ሴኬንያ ከእጁ በታች ነበሩ።
16ከሦስትም ዓመት ወደ ላይ ላሉ በየሰሞናቸው ለሥራቸውና ለአገልግሎታቸው ዕለት ዕለት ወደ እግዚአብሔር ቤት ለሚገቡ ወንዶች ሁሉ፤
17በየአባቶቻቸውም ቤት ለተቈጠሩ ካህናት፥ ከሀያ ዓመትም ወደ ላይ ላሉ በየሥርዓታቸውና በየሰሞናቸው ለተቈጠሩ ሌዋውያን፥
18በማኅበሩም ሁሉ በየትውልዳቸው ለተቈጠሩ ለሕፃናቶቻቸውና ለሚስቶቻቸው ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቻቸውም ይሰጡ ነበር፤ በእምነት ተቀድሰዋልና።
19በየከተማይቱም ሁሉ በከተማቸው መሰምርያዎቹ ላሉ ለአሮን ልጆች ለካህናቱ፥ ከካህናቱም ወገን ላሉ ወንዶች ሁሉ፥ በትውልዳቸውም ለተቈጠሩ ሌዋውያን ሁሉ ክፍላቸውን ይሰጡ ዘንድ በስማቸው የተጻፉ ሰዎች ነበሩ።
20ሕዝቅያስም በይሁዳ ሁሉ እንዲህ አደረገ፤ በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት መልካምንና ቅንን ነገር እውነትንም አደረገ።
21ስለ እግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት በጀመረው ሥራ ሁሉ፥ በሕጉና በትእዛዙም፥ አምላኩን ለመፈለግ በፍጹም ልቡ አደረገው፥ ተከናወነለትም። ቸ