English

ምዕራፍ 34

1ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ።
2በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፥ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም።
3በነገሠም በስምንተኛው ዓመት ገና ብላቴና ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ ይፈልግ ጀመር፤ በአሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኮረብታው መስገጃዎችና ከማምለኪያ ዐፀዶቹ፥ ከተቀረጹትና ቀልጠው ከተሠሩት ምስሎች ያነጻ ጀመር።
4የበኣሊምንም መሠዊያዎች በፊቱ አፈረሱ፤ በላዩም የነበሩትን የፀሐዩን ምስሎች የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የተቀረጹትንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች ሰባበረ፥ አደቀቃቸውም፥ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብርም ላይ በተናቸው።
5የካህናቶቻቸውንም አጥንት በመሠዊያቸው ላይ አቃጠለ፤ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አንጻ።
6የምናሴንና የኤፍሬምንም የስምዖንና የንፍታሌምንም ከተሞች፥ በዙሪያቸውም ያለውን ቦታ እንዲሁ አነጻ።
7መሠዊያዎቹንም አፈረሰ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንና የተቀረጹትን ምስሎች አደቀቀ፥ በእስራኤልም አገር ሁሉ የፀሐይን ምስሎች ሁሉ ቈራረጠ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ።
8በነገሠም በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ምድሪቱንና የእግዚአብሔርን ቤት ካነጻ በኋላ፥ የኤዜልያስ ልጅ ሳፋን፥ የከተማይቱም አለቃ መዕሤያ፥ ታሪክ ጸሐፊም የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአክ የእግዚአብሔርን የአምላኩን ቤት ይጠግኑ ዘንድ ሰደዳቸው።
9ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኬልቅያስ መጡ፤ ሌዋውያኑም በረኞች ከምናሴና ከኤፍሬም ከቀረውም ከእስራኤል ሁሉ፥ ከይሁዳና ከብንያም ሁሉ በኢየሩሳሌምም ከሚኖሩት የሰበሰቡትን፥ ወደ እግዚእብሔር ቤት የቀረበውን ገንዘብ ሰጡት።
10የእግዚአብሔርንም ቤት በሚሠሩት ላይ ለተሾሙት ሰጡ፤ እነርሱም ይጠግኑና ያድሱ ዘንድ፥ የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠሩ ሠራተኞች ሰጡ።
11የይሁዳ ነገሥታት ላፈረሱት ቤት ሰረገሎች ያደርጉ ዘንድ፥ ለማጋጠሚያም እንጨት የተጠረበውንም ድንጋይ ይገዙ ዘንድ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች ሰጡ።
12ሰዎቹም ሥራውን በመታመን አደረጉ፤ በእነርሱም ላይ የተሾሙት፥ ሥራውንም የሚያሠሩት ሌዋውያን ከሜራሪ ልጆች ኢኤትና አብድዩ፥ ከቀዓትም ልጆች ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን በዜማ ዕቃ አዋቂዎች የነበሩ ሁሉ
13በተሸካሚዎችና ልዩ ልዩ ሥራ በሚሠሩ ላይ ተሾመው ነበር፤ ጸሐፊዎቹና አለቆቹም በረኞቹም ከሌዋውያን ወገን ነበሩ።
14ወደ እግዚአብሔርም ቤት የቀረበውን ገንዘብ ባመጡ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስም በሙሴ እጅ የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ።
15ኬልቅያስም ጸሐፊውን ሳፋንን። የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቼአለሁ ብሎ ተናገረው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው።
16ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ አመጣ፤ ለንጉሡም። ባሪያዎችህ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ሁሉ ያደርጋሉ፤
17በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን ገንዘብ አፈሰሱ፥ በሥራውም ላይ ለተሾሙትና ለሠራተኞቹ ሰጡ ብሎ አወራለት።
18ጸሐፊውም ሳፋን ለንጉሡ። ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጠኝ ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው።
19ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ።
20ንጉሡም ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ ዓብዶንን፥ ጸሐፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዓሳያን።
21በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ፥ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ለእኔ በእስራኤልና በይሁዳም ለቀሩት እግዚአብሔርን ጠይቁ ብሎ አዘዛቸው።
22ኬልቅያስና እነዚያ ንጉሥ ያዘዛቸው ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቲቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በከተማይቱ በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ይህንም ነገር ነገሩአት።
23እርስዋም አለቻቸው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት።
24እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ፥ ማለት ክፉ ነገርን፥ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ አመጣለሁ።
25በእጃቸው ሥራ ሁሉ ሊያስቈጡኝ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት ዐጥነዋልና ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ይነድዳል፥ አይጠፋምም።
26እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ ሰማኸው ቃል ልብህ ገር ሆኖአልና፥
27በፊቴም ራስህን አዋርደሃልና፥ በዚህም ስፍራና በሚኖሩበት ላይ ቃሌን በሰማህ ጊዜ ራስህን አዋርደሃልና፥ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ አለቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼአለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
28እነሆ፥ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፥ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ ዓይኖችህ አያዩም። ይህንም ለንጉሥ አወሩለት።
29ንጉሡም ላከ፥ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምንም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰበ።
30ንጉሡም የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ በጆሮአቸው አነበበ።
31ንጉሡም በስፍራው ቆሞ እግዚአብሔርን ተከትሎ እንዲሄድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩን ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ እንዲጠብቅ፥ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል እንዲያደርግ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ።
32በኢየሩሳሌምና በብንያምም የተገኙትን ሁሉ በዚህ ነገር አማለ፤ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት የአባቶቻቸው አምላክ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እንዳዘዘ አደረጉ።
33ኢዮስያስም ከእስራኤል ልጆች ምድር ሁሉ ርኩሱን ሁሉ አስወገደ፥ በእስራኤልም የተገኙትን ሁሉ አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አደረገ። በዘመኑ ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ከመከተል አልራቁም።