ምዕራፍ 32
1እነሆ፥ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፥ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ።
2ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፥ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፥ በበረሃም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል።
3የሚያዩትም ሰዎች ዓይኖች አይጨፈኑም፥ የሚሰሙትም ጆሮች ያደምጣሉ።
4ጥንቃቄ የሌላቸው ሰዎች ልብ እውቀትን ታስተውላለች፥ የተብታቦችም ምላስ ደኅና አድርጋ ትናገራለች።
5ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍ ከበርቴ ተብሎ አይጠራም፥ ንፉግም ለጋስ አይባልም።
6ሰነፍ ግን ስንፍናን ይናገራል፥ ልቡም ዝንጉነትን ይፈጽም ዘንድ በእግዚአብሔርም ላይ ስሕተትን ይናገር ዘንድ የተራበችውንም ሰውነት ባዶ ያደርግ ዘንድ ከተጠማም ሰው መጠጥን ይቈርጥ ዘንድ በደልን ይሠራል።
7የንፉግም ዕቃ ክፉ ናት፤ ችግረኛ ቅን ነገርን በተናገረ ጊዜ እንኳ እርሱ በሐሰት ቃል ድሀውን ያጠፋ ዘንድ ክፉን አሳብ ያስባል።
8ከበርቴ ሰው ግን ለመከበር ያስባል፥ በመከበርም ጸንቶ ይኖራል።
9እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፥ ተነሡ ድምፄንም ስሙ፤ እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ልጆች ሆይ፥ ንግግሬን አድምጡ።
10እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ሆይ፥ ወይንን መቍረጥ ይጠፋልና፥ ፍሬም ማከማቸት አይመጣምና ከዓመትና ከጥቂት ቀን በኋላ ትንቀጠቀጣላችሁ።
11እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፥ ተጠንቀቁ፤ ተማምናችሁም የምትቀመጡ ሆይ፥ ተንቀጥቀጡ፤ ልብሳችሁን አውልቁ፥ ዕራቁታችሁን ሁኑ፥ ወገባችሁንም በማቅ ታጠቁ።
12ስለ ተወደደችውም እርሻ ስለሚያፈራውም ወይን ደረታችሁን ድቁ።
13በሕዝቤ ምድር ላይ፥ በደስታ ከተማ ባሉት በደስታ ቤቶች ሁሉ ላይ እሾህና ኵርንችት ይወጣባቸዋል፤
14አዳራሹ ወና ትሆናለችና፥ የብዙ ሰውም ከተማ ትለቀቃለችና፥ አምባውና ግንቡም ለዘላለም ዋሻ፥ የምድረ በዳም አህያ ደስታ፥ የመንጎችም ማሰማርያ ይሆናልና።
15ይህም፥ መንፈስ ከላይ እስኪፈስስልን፥ ምድረ በዳውም ፍሬያማ እርሻ እስኪሆን፥ ፍሬያማውም እርሻ ዱር ተብሎ እስኪቈጠር ድረስ ይሆናል።
16ከዚያ በኋላ ፍርድ በምድረ በዳ ይኖራል፥ ጽድቅም በፍሬያማው እርሻ ያድራል።
17የጽድቅም ሥራ ሰላም፥ የጽድቅም ፍሬ ለዘላለም ጸጥታና መታመን ይሆናል።
18ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል።
19በረዶ ግን በዱር ላይ ይወርዳል፥ ከተማም ፈጽማ ትዋረዳለች።
20እናንተ የበሬና የአህያ እግር እየነዳችሁ በውኃ ሁሉ አጠገብ የምትዘሩ ብፁዓን ናችሁ።