ምዕራፍ 41
1ደሴቶች ሆይ፥ በፊቴ ዝም በሉ፤ አሕዛብም ኃይላቸውን ያድሱ፤ ይቅረቡም በዚያን ጊዜም ይናገሩ፤ ለፍርድ ለአንድነት እንቅረብ።
2ከምሥራቅ አንዱን ያስነሣ በጽድቅም ወደ እግሩ የተጠራው ማን ነው? አሕዛብንም አሳልፎ በፊቱ ሰጠው፥ ነገሥታትንም አስገዛለት፤ ለሰይፉ እንደ ትቢያ ለቀስቱም እንደ ተጠረገ እብቅ አድርጎ ሰጣቸው።
3አሳደዳቸው፥ እግሮቹም አስቀድመው ባልሄዱባት መንገድ በደኅነት አለፈ።
4ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር፥ ፊተኛው በኋላኞችም ዘንድ የምኖር እኔ ነኝ።
5ደሴቶች አይተው ፈሩ፥ የምድርም ዳርቾች ተንቀጠቀጡ፤ ቀረቡም ደረሱም።
6ሁሉም እያንዳንዱ ባልንጀራውን ይረዳው ነበር፥ ወንድሙንም። አይዞህ ይለው ነበር።
7አናጢውም አንጥረኛውን፥ በመዶሻም የሚያሳሳውን መስፍ መችውን አጽናና፥ ስለ ማጣበቅ ሥራውም። መልካም ነው አለ፤ እንዳይንቀሳቀስም በችንካር አጋጠመው።
8ባሪያዬ እስራኤል፥ የመረጥሁህ ያዕቆብ፥ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፥
9አንተ ከምድር ዳርቻ የያዝሁህ ከማዕዘንዋም የጠራሁህና። አንተ ባሪያዬ ነህ፥ መርጬሃለሁ አልጥልህም ያልሁህ ሆይ፥
10እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።
11እነሆ የሚቆጡህ ሁሉ ያፍራሉ፥ ይዋረዱማል፤ የሚከራከሩህም እንዳልነበሩ ይሆናሉ፥ ይጠፉማል።
12የሚያጣሉህንም ትሻቸዋለህ አታገኛቸውምም፥ የሚዋጉህም እንዳልነበሩና እንደ ምናምን ይሆናሉ።
13እኔ አምላክህ እግዚአብሔር። አትፍራ፥ እረዳሃለሁ ብዬ ቀኝህን እይዛለሁና።
14አንተ ትል ያዕቆብ የእስራኤልም ሰዎች ሆይ፥ አትፍሩ፤ እረዳሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው።
15እነሆ፥ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፤ ተራሮችንም ታሄዳለህ ታደቅቃቸውማለህ፥ ኮረብቶችንም እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ።
16ታበጥራቸዋለህ፥ ነፋስም ይጠርጋቸዋል፥ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ አንተም በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፥ በእስራኤልም ቅዱስ ትመካለህ።
17ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፥ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፤ እኔ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፥ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም።
18በወናዎቹ ኮረብቶች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፤ ምድረ በዳውን ለውኃ መቆሚያ፥ የጥማትንም ምድር ለውኃ መፍለቂያ አደርጋለሁ።
19
20የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንደ ሠራች፥ የእስራኤልም ቅዱስ እንደ ፈጠረው ያዩ ዘንድ ያውቁም ዘንድ ያስቡም ዘንድ በአንድነትም ያስተውሉ ዘንድ፥ በምድረ በዳ ዝግባውንና ግራሩን ባርሰነቱንና የዘይቱን ዛፍ አበቅላለሁ፥ በበረሀውም ጥዱንና አስታውን ወይራውንም በአንድነት አኖራለሁ።
21ክርክራችሁን አቅርቡ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ማስረጃችሁን አምጡ፥ ይላል የያዕቆብ ንጉሥ።
22ያምጡ፥ የሚሆነውንም ይንገሩን፤ ልብም እናደርግ ዘንድ ፍጻሜአቸውንም እናውቅ ዘንድ፥ የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ተናገሩ፥ የሚመጡትንም አሳዩን።
23አማልክትም መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ በኋላ የሚመጡትን ተናገሩ፤ እንደነግጥም ዘንድ በአንድነትም እናይ ዘንድ መልካሙን ወይም ክፉውን አድርጉ።
24እነሆ፥ እንዳልነበረ ናችሁ፥ ሥራችሁም ከንቱ ነው፤ የሚመርጣችሁም አስጻያፊ ነው።
25አንዱን ከሰሜን አነሣሁ መጥቶአልም፤ አንዱም ከፀሐይ መውጫ ስሜን የሚጠራ ይመጣል፤ በጭቃ ላይ እንደሚመጣ ሰው አፈርም እንደሚረግጥ ሸክለኛ በአለቆች ላይ ይመጣል።
26እናውቅ ዘንድ ከጥንት የተናገረው። እውነት ነው እንልም ዘንድ ቀድሞ የተናገረው ማን ነው? የሚናገር የለም፥ የሚገልጥም የለም፥ ቃላችሁንም የሚሰማ የለም።
27በመጀመሪያ ለጽዮን። እነኋቸው እላለሁ፤ ለኢየሩሳሌምም የምስራች ነጋሪን እሰጣለሁ።
28ብመለከት ማንም አልነበረም፤ ብጠይቃቸውም የሚመልስልኝ አማካሪ በመካከላቸው የለም።
29እነሆ፥ እነርሱ ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፥ ሥራቸውም ምንምን ናት፤ ቀልጠው የተሠሩት ምስሎቻቸውም ነፋስና ኢምንት ናቸው።