English

ምዕራፍ 5

1አሁን ስለ ወዳጄና ስለ ወይን ቦታው ለወዳጄ ቅኔ እቀኛለሁ። ለወዳጄ በፍሬያማው ኮረብታ ላይ የወይን ቦታ ነበረው።
2በዙሪያው ቈፈረ፥ ድንጋዮችንም ለቅሞ አወጣ፥ ምርጥ የሆነውንም አረግ ተከለበት፥ በመካከሉም ግንብ ሠራ፥ ደግሞም የመጥመቂያ ጕድጓድ ማሰበት፤ ወይንንም ያፈራ ዘንድ ተማመነ፥ ዳሩ ግን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ።
3አሁንም እናንተ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሆይ፥ በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል እስኪ ፍረዱ።
4ለወይኔ ያላደረግሁለት፥ ከዚህ ሌላ አደርግለት ዘንድ የሚገባኝ ምንድር ነው? ወይንን ያፈራል ብዬ ስትማመን ስለ ምን ሆምጣጣ ፍሬ አፈራ?
5አሁንም በወይኔ ላይ የማደርገውን እነግራችኋለሁ፤ አጥሩን እነቅላለሁ፥ ለማሰማርያም ይሆናል፤ ቅጥሩንም አፈርሳለሁ፥ ለመራገጫም ይሆናል።
6ባድማ አደርገዋለሁ፤ አይቈረጥም፥ አይኰተኰትም፤ ኵርንችትና እሾህ ይበቅልበታል፤ ዝናብንም እንዳያዘንቡበት ዳመናዎችን አዝዛለሁ።
7የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ወይን ቦታ እርሱ የእስራኤል ቤት ነው፥ የደስታውም አትክልት የይሁዳ ሰዎች ናቸው፤ ፍርድን ተስፋ ያደርግ ነበር፥ እነሆም ደም ማፍሰስ ሆነ፤ ጽድቅንም ይተማመን ነበር፥ እነሆም፥ ጩኸት ሆነ።
8ስፍራ እስከማይቀር ድረስ እናንተም በምድር ላይ ብቻችሁን እስክትቀመጡ ድረስ፥ ቤትን ከቤት ጋር ለሚያያይዙ እርሻንም ከእርሻ ጋር ለሚያቀራርቡ ወዮላቸው!
9የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጆሮዬ እንዲህ አለ። በእውነት ብዙ ታላቅና መልካም ቤት ባድማ ይሆናል፥ የሚቀመጥበትም አይገኝም።
10ከወይኑ ቦታ አሥር ጥማድ በሬ ካረሰው አንድ የባዶስ መስፈሪያ ብቻ ይወጣል፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ዘር አንድ የኢፍ መስፈሪያ ብቻ ይሰጣል።
11ስካርን ለመከተል በጥዋት ለሚማልዱ፥ የወይን ጠጅም እስኪያቃጥላቸው እስከ ሌሊት ድረስ ለሚዘገዩ ወዮላቸው!
12መሰንቆና በገና ከበሮና እምቢልታም የወይን ጠጅም በግብዣቸው አለ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ ግን አልተመለከቱም፥ እጁም ያደረገችውን አላስተዋሉም።
13ስለዚህ ሕዝቤ ወደ ምርኮ ሄዱ፥ ጌታን አላወቁትምና፤ ከበርቴዎቻቸውም ተራቡ፥ ሕዝባቸውም ተጠሙ።
14ሲኦልም ሆድዋን አስፍታለች፥ አፍዋንም ያለ ልክ ከፍታለች፤ ከበርቴዎቻቸውና አዛውንቶቻቸው ባለጠጎቻቸውም ደስተኞቻቸውም ወደ እርስዋ ይወርዳሉ።
15ሰውም ይጐሰቍላል፥ ሰውም ይዋረዳል፥ የትዕቢተኞችም ዓይን ትዋረዳለች፤
16የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን በፍርድ ከፍ ከፍ ብሎአል፥ ቅዱሱም አምላክ በጽድቅ ተቀድሶአል።
17የበግ ጠቦቶች በማሰማርያቸው ውስጥ ይሰማራሉ፥ እንግዶችም የሰቡትን ባድማ ይበላሉ።
18በደልን በምናምንቴ ገመድ፥ ኃጢአትንም በሰረገላ ማሰሪያ ወደ ራሳቸው ለሚስቡ። እናይ ዘንድ ይቸኵል፥
19ሥራውንም ያፋጥን፤ እናውቃትም ዘንድ የእስራኤል ቅዱስ ምክር ትቅረብ፥ ትምጣ ለሚሉ ወዮላቸው!
20ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፥ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!
21በዓይናቸው ጥበበኞች በነፍሳቸውም አስተዋዮች ለሆኑ ወዮላቸው!
22የወይን ጠጅ ለመጠጣት ኃያላን የሚያሰክረውንም ለማደባለቅ ጨካኞች ለሆኑ፤
23በደለኛውን ስለ ጉቦ ጻድቅ ለሚያደርጉ፥ የጻድቁንም ጽድቅ ለሚያስወግዱበት ወዮላቸው!
24ስለዚህ የእሳት ወላፈን ቃርሚያን እንደሚበላ፥ እብቅም በነበልባል ውስጥ እንደሚጠፋ፥ እንዲሁ የእነርሱ ሥር የበሰበሰ ይሆናል ቡቃያቸውም እንደ ትቢያ ይበንናል፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ጥለዋልና፥ የእስራኤልም ቅዱስ የተናገረውን ቃል አቃልለዋልና።
25ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነድዶአል እጁንም በላያቸው ዘርግቶ መትቶአቸዋል፤ ተራሮችም ተንቀጠቀጡ፥ ሬሳቸውም በአደባባይ መካከል እንደ ጕድፍ ሆኖአል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
26ለአሕዛብም በሩቅ ምልክትን ያቆማል፥ ከምድርም ዳርቻ በፉጨት ይጠራቸዋል፤ እነሆም፥ እየተጣደፉ ፈጥነው ይመጣሉ።
27ደካማና ስንኵል የለባቸውም፥ የሚያንቀላፋና የሚተኛም የለም፤ የወገባቸውም መቀነት አይፈታም፥ የጫማቸውም ማዘቢያ አይበጠስም።
28ፍላጾቻቸው ተስለዋል፥ ቀስቶቻቸውም ሁሉ ተለጥጠዋል፤ የፈረሶቻቸውም ኮቴ እንደ ቡላድ የሰረገሎቻቸውም መንኰራኵር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይቈጠራል።
29ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፥ እንደ አንበሳ ደቦሎችም ያገሣሉ፤ ንጥቂያንም ይዘው ያገሣሉ፥ ይወስዱትማል፥ የሚያድንም የለም።
30በዚያም ቀን እንደ ባሕር መትመም ይተምሙባቸዋል፤ ወደ ምድርም ቢመለከቱ፥ እነሆ፥ ጨለማና መከራ አለ፤ ብርሃንም በደመናዎችዋ ውስጥ ጨልሞአል።