English

ምዕራፍ 54

1አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ፥ ዘምሪ፤ አንቺ ያላማጥሽ ሆይ፥ እልል በዪ፥ ጩኺም፤ ባል ካላት ይልቅ ፈት የሆነቺቱ ልጆች በዝተዋልና፥ ይላል እግዚአብሔር።
2የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፥ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቈጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ።
3በቀኝና በግራ ትሰፋፊያለሽና፥ ዘርሽም አሕዛብን ይወርሳልና፥ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ያደርጋልና።
4አታፍሪምና አትፍሪ፤ አተዋረጂምና አትደንግጪ፤ የሕፃንነትሽንም እፍረት ትረሺዋለሽ፥ የመበለትነትሽንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አታስቢም።
5ፈጣሪሽ ባልሽ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ የእስራኤልም ቅዱስ ታዲጊሽ ነው፥ እርሱም የምድር ሁሉ አምላክ ይባላል።
6እግዚአብሔር እንደ ተተወችና እንደ ተበሳጨች በልጅነትዋም እንደ ተጣለች ሚስት ጠርቶሻል፥ ይላል አምላክሽ።
7ጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፥ በታላቅም ምሕረት እሰበስብሻለሁ።
8በጥቂት ቍጣ ለቅጽበት ዓይን ፊቴን ከአንቺ ሰወርሁ፥ በዘላለምም ቸርነት እምርሻለሁ፥ ይላል ታዳጊሽ እግዚአብሔር።
9ይህ ለእኔ እንደ ኖኅ ውኃ ነው፤ የኖኅ ውኃ ደግሞ በምድር ላይ እንዳያልፍ እንደ ማልሁ፥ እንዲሁ አንቺን እንዳልቈጣ እንዳልዘልፍሽም ምያለሁ።
10ተራሮች ይፈልሳሉ፥ ኮረብቶችም ይወገዳሉ፤ ቸርነቴ ግን ከአንቺ ዘንድ አይፈልስም የሰላሜም ቃል ኪዳን አይወገድም፥ ይላል መሐሪሽ እግዚአብሔር።
11አንቺ የተቸገርሽ በዐውል ነፋስም የተናወጥሽ ያልተጽናናሽም፥ እነሆ፥ ድንጋዮችሽን ሸላልሜ እገነባለሁ፥ በሰንፔርም እመሠርትሻለሁ።
12የግንብሽንም ጕልላት በቀይ ዕንቍ፥ በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ዳርቻሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ።
13ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል።
14በጽድቅ ትታነጺያለሽ፤ ከግፍ ራቂ፥ አትፈሪምም፥ ድንጋጤም ወደ አንቺ አትቀርብም።
15እነሆ፥ ይሰበሰባሉ፥ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም፤ በአንቺም ላይ የሚሰበሰቡ ሁሉ ከአንቺ የተነሣ ይወድቃሉ።
16እነሆ፥ ፍሙን በወናፍ የሚያናፋ ለሥራውም መሣሪያ የሚያወጣ ብረት ሠሪን እኔ ፈጥሬአለሁ፤ የሚያፈርሰውንም እንዲያጠፋ ፈጥሬአለሁ።
17በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፥ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር።