ምዕራፍ 4
1ይህም ዮናስን ከቶ ደስ አላሰኘውም፥ እርሱም ተቈጣ።
2ወደ እግዚአብሔርም ጸለየና። አቤቱ፥ እለምንሃለሁ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር።
3አሁንም፥ አቤቱ፥ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፥ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ አለው።
4እግዚአብሔርም። በውኑ ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን? አለ።
5ዮናስም ከከተማይቱ ወጣ፥ ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ተቀመጠ፤ ከተማይቱንም የሚያገኛትን እስኪያይ ድረስ በዚያ ለራሱ ዳስ ሠርቶ ከጥላው በታች ተቀመጠ።
6እግዚአብሔር አምላክም ቅል አዘጋጀ፥ ከጭንቀቱም ታድነው ዘንድ በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን በዮናስ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት፤ ዮናስም ስለ ቅሊቱ እጅግ ደስ አለው።
7በነጋው ግን ወገግ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዘጋጀ፥ እርስዋም ቅሊቱን እስክትደርቅ ድረስ መታቻት።
8ፀሐይም በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ትኩስ የምሥራቅ ነፋስ አዘጋጀ ዮናስ እስኪዝል ድረስም ፀሐይ ራሱን መታው፤ ለራሱም ሞትን ፈለገና። ከሕይወት ሞት ይሻለኛል አለ።
9እግዚአብሔርም ዮናስን። በውኑ ስለዚች ቅል ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን? አለው። እርሱም። እስከ ሞት ድረስ እቈጣ ዘንድ ይገባኛል አለ።
10እግዚአብሔርም። አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፥ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል።
11እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን? አለው።