English

ምዕራፍ 10

1[see v2]
2እግዚአብሔርም ሙሴን። እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በግብፃውያን ያደረግሁትን ነገር ያደረግሁባቸውንም ተአምራቴን በልጅህ በልጅ ልጅህም ጆሮች ትነግር ዘንድ፥ ይህችንም ተአምራቴን በመካከላቸው አደረግ ዘንድ የእርሱን የባሪያዎቹንም ልብ አደንድኜአለሁና ወደ ፈርዖን ግባ አለው።
3ሙሴም አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ አሉትም። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በፊቴ ለመዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
4ሕዝቤን ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን፥ እነሆ ነገ በአገርህ አንበጣዎችን አመጣለሁ፤
5የምድሩንም ፊት ይሸፍኑታልና ምድሩን ለማየት አይቻልም፤ ከበረዶውም አምልጦ የተረፈላችሁን ትርፍ ይበሉታል፥ ያደገላችሁንም የእርሻውን ዛፍ ሁሉ ይበሉታል፤
6ቤቶችህም የባሪያዎችህም ሁሉ ቤቶች የግብፃውያንም ሁሉ ቤቶች በእነርሱ ይሞላል፤ አባቶችህ የአባቶችህም አባቶች በምድር ላይ ከተቀመጡበት ቀን ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያላዩት ነው። ተመልሶም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ።
7የፈርዖንም ባሪያዎች። ይህ ሰው እስከ መቼ ዕንቅፋት ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ሰዎችን ልቀቅ ግብፅስ እንደ ጠፋች ገና አታውቅምን? አሉት።
8ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን መልሶ አስመጣቸው። ሂዱ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ ነገር ግን የሚሄዱት እነማን ናቸው? አላቸው።
9ሙሴም። እኛ እንሄዳለን፥ የእግዚአብሔር በዓል ሆኖልናልና ታናናሾቻችንና ሽማግሌዎቻችን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም በጎቻችንና ከብቶቻችንም ከእኛ ጋር ይሄዳሉ አለ።
10ፈርዖንም። እናንተን ከልጆቻችሁ ጋር ስለቅቅ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ ነገር ግን ክፉ ነገር በፊታችሁ እንደሚሆን ተመልከቱ።
11እንዲህም አይይደለም፤ እናንተ ወንዶቹ ሂዱ፥ ይህን ፈልጋችኋልና እግዚአብሔርን አገልግሉ አላቸው። ከፈርዖንም ፊት አባረሩአቸው።
12እግዚአብሔርም ሙሴን። በግብፅ አገር ላይ እንዲወጡ፥ ከበረዶውም የተረፈውን የምድርን ቡቃያ ሁሉ እንዲበሉ፥ ስለ አንበጣዎች በግብፅ አገር ላይ እጅህን ዘርጋ አለው።
13ሙሴም በግብፅ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፥ እግዚአብሔርም የምሥራቅን ነፋስ ያን ቀን ሁሉ ሌሊቱን ሁሉ አመጣ፤ ማለዳም በሆነ ጊዜ የምሥራቁ ነፋስ አንበጣዎቹን አመጣ።
14አንበጣዎችም በግብፅ አገር ሁሉ ላይ ወጡ፥ በግብፅም ዳርቻ ሁሉ ላይ ተቀመጡ፤ እጅግም ብዙ ነበሩ፤ ይህንም የሚያህል አንበጣ በፊት አልነበረም፥ ወደ ፊትም ደግሞ እንደ እርሱ አይሆንም።
15የምድሩንም ፊት ፈጽመው ሸፈኑት አገሪቱም ጨለመች፤ የአገሪቱን ቡቃያ ሁሉ በረዶውም የተወውን በዛፉ የነበረውን ፍሬ ሁሉ በሉ፤ ለምለም ነገር ዛፍም የምድር ሣርም በግብፅ አገር ሁሉ አልቀረም።
16ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በፍጥነት ጠራ። አምላካችሁን እግዚአብሔርን እናንተንም በደልሁ፤
17አሁን እንግዲህ በዚህ ጊዜ ብቻ ኃጢአቴን ይቅር በሉኝ፥ ይህንም ሞት ብቻ ከእኔ ያነሣልኝ ዘንድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለምኑ አላቸው።
18ሙሴም ከፈርዖን ፊት ወጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመነ።
19እግዚአብሔርም ከምዕራብ ዐውሎ ነፋሱን አስወገደ፥ አንበጣዎችንም ወስዶ በኤርትራ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤ አንድ አንበጣም በግብፅ ዳርቻ ሁሉ አልቀረም።
20እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና የእስራኤልንም ልጆች አልለቀቀም።
21እግዚአብሔርም ሙሴን። እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ላይ ሰው የሚዳስሰው ፅኑ ጨለማ ይሁን አለው።
22ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፥ በግብፅም አገር ሁሉ ላይ ፅኑ ጨለማ ሦስት ቀን ሆነ፤
23ማንም ወንድሙን አላየም፥ ሦስት ቀንም ሙሉ ከስፍራው ማንም አልተነሣም፤ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ግን በተቀመጡበት ስፍራ ብርሃን ነበራቸው።
24ፈርዖንም ሙሴን ጠርቶ። ሂዱ፥ እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ ነገር ግን በጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ተዉ፤ ልጆቻችሁ ደግሞ ከእናንተ ጋር ይሂዱ አለው።
25ሙሴም። አንተ ደግሞ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የምንሠዋው መሥዋዕትንና የሚቃጠል መሥዋዕትን ትሰጠናለህ።
26አምላካችንን እግዚአብሔርን ለማገልገል ከእነርሱ እንወስዳለንና ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ፥ አንድ ሰኮናም አይቀርም፤ አምላካችን የምናገለግለው ምን እንደሆነ ከዚያ እስክንደርስ አናውቅም አለ።
27እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና፥ ሊለቅቃቸውም አልወደደም።
28ፈርዖንም። ከእኔ ዘንድ ሂድ፤ ፊቴን ባየህበት ቀን ትሞታለህና ፊቴን እንዳታይ ተጠንቀቅ አለው።
29ሙሴም። እንደ ተናገርህ ይሁን፤ ፊትህን እንደ ገና አላይም አለ።