ምዕራፍ 32
1ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው። ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት።
2አሮንም። በሚስቶቻችሁ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁም ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ አላቸው።
3ሕዝቡም ሁሉ በጆሮቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብረው ወደ አሮን አመጡለት።
4ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አላቸው።
5አሮንም ባየው ጊዜ መሠዊያን በፊቱ ሠራ፤ አሮንም።ነገ የእግዚአብሔር በዓል ነው ሲል አወጀ።
6በነጋውም ማልደው ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፥ የደኅነትም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፥ ሊዘፍኑም ተነሡ።
7እግዚአብሔርም ሙሴን። ከግብፅ ምድር ያወጣኸው ሕዝብህ ኃጢአት ሠርተዋልና ሂድ፥ ውረድ።
8ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አደረጉ፥ ሰገዱለትም፥ ሠዉለትም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አሉ ሲል ተናገረው።
9እግዚአብሔርም ሙሴን። እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት፥ እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው።
10አሁንም ቍጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ፤ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው።
11ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፥ አለም። አቤቱ፥ ቍጣህ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ስለ ምን ተቃጠለ?
12ግብፃውያንስ። በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ።
13ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ።
14እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ።
15ሙሴም ተመለሰ፥ ሁለቱንም የምስክር ጽላቶች በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቶቹም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር።
16ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቶች ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ።
17ኢያሱም እልል ሲሉ የሕዝቡን ድምፅ ሰምቶ ሙሴን። የሰልፍ ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ አለ አለው።
18እርሱም። ይህ የድል ነሺዎች ወይም የድል ተነሺዎች ድምፅ አይደለም፥ ነገር ግን የዘፈን ድምፅ እሰማለሁ አለው።
19እንዲህም ሆነ፤ ወደ ሰፈሩ ሲቀርብ ጥጃውንም ዘፈኑንም አየ፤ የሙሴም ቍጣ ተቃጠለ፥ ጽላቶቹንም ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች ሰበራቸው።
20የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፥ እንደ ትቢያም እስኪሆን ድረስ ፈጨው፥ በውኃውም ላይ በተነው፥ ለእስራኤልም ልጆች አጠጣው።
21ሙሴም አሮንን። ይህን ታላቅ ኃጢአት ታመጣበት ዘንድ ይህ ሕዝብ ምን አደረገህ? አለው።
22አሮንም እንዲህ አለ። ጌታዬ ሆይ፥ ቍጣህ አይቃጠል፤ ይህ ሕዝብ ክፋትን እንዲወድድ አንተ ታውቃለህ።
23እነርሱም። ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉኝ።
24እኔም። ከእናንተ ወርቅ ያለው ሰው ከእርሱ ሰብሮ ያምጣልኝ አልኋቸው፤ ሰጡኝም፤ በእሳትም ላይ ጣልሁት፥ ይህም ጥጃ ወጣ።
25ሙሴም በጠላቶቻቸው ፊት እንዲነወሩ አሮን ስድ ለቅቋቸዋልና ሕዝቡ ስድ እንደ ተለቀቁ ባየ ጊዜ፥
26በሰፈሩ ደጅ ቆሞ። የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ! አለ፤ የሌዊም ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ።
27እርሱም። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእናንተ ሰው ሁሉ ሰይፉን በወገቡ ላይ ይታጠቅ፥ በሰፈሩም ውስጥ በዚህና በዚያ ከበር እስከ በር ተመላለሱ፥ የእናንተም ሰው ሁሉ ወንድሙን ወዳጁንም ጎረቤቱንም ይግደል አላቸው።
28የሌዊም ልጆች ሙሴ እንዳለ አደረጉ፤ በዚያም ቀን ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ሰዎች ሞቱ።
29ሙሴም። ዛሬ በረከትን እንዲያወርድላችሁ እያንዳንዳችሁ በልጃችሁና በወንድማችሁ ላይ ዛሬ እጃችሁን ለእግዚአብሔር ቅዱስ አድርጉ አለ።
30በነጋውም ሙሴ ለሕዝቡ። እናንተ ታላቅ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ አሁንም ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤ ምናልባት ኃጢአታችሁን አስተሰርይላችኋለሁ አላቸው።
31ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ። ወዮ! እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤
32አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለ።
33እግዚአብሔርም ሙሴን። የበደለኝን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ።
34አሁንም ሂድ፥ ይህንም ሕዝብ ወደ ነገርሁህ ምራ፤ እነሆ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምጐበኝበት ቀን ኃጢአታቸውን አመጣባቸዋለሁ አለው።
35አሮን የሠራውን ጥጃ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ቀሠፈ።