ምዕራፍ 15
1ከዚህ ነገር በኋላም የእግዚአብሔር ቃል በራእይ ወደ አብራም መጣ፥ እንዲህ ሲል። አብራም ሆይ፥ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው።
2አብራምም። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ ምንን ትሰጠኛለህ? እኔም ያለ ልጅ እሄዳለሁ፤ የቤቴም መጋቢ የደማስቆ ሰው ይህ ኤሊዔዘር ነው አለ።
3አብራምም። ለእኔ ዘር አልሰጠኸኝም፤ እነሆም፥ በቤቴ የተወለደ ሰው ይወርሰኛል አለ።
4እነሆም፥ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት። ይህ አይወርስህም፤ ነገር ግን ከጉልበትህ የሚወጣው ይወርስሃል።
5ወደ ሜዳም አወጣውና። ወደ ሰማይ ተመልከት፥ ከዋክብትንም ልትቈጥራቸው ትችል እንደ ሆነ ቍጠር አለው። ዘርህም እንደዚሁ ይሆናል አለው።
6አብራምም በእግዚአብሔር አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት።
7ይህችን ምድር ትወርሳት ዘንድ እንድሰጥህ ከከለዳውያን ዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ አለው።
8አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድወርሳት በምን አውቃለሁ? አለ።
9እርሱም። የሦስት ዓመት ጊደር፥ የሦስት ዓመት ፍየልም፥ የሦስት ዓመት በግም፥ ዋኖስም፥ ርግብም ያዝልኝ አለው።
10እነዚህንም ሁሉ ወሰደለት፥ በየሁለትም ከፈላቸው፥ የተከፈሉትንም በየወገኑ ትይዩ አደረጋቸው፤ ወፎችን ግን አልከፈለም።
11አሞራዎችም በሥጋው ላይ ወረዱ፥ አብራምም አበረራቸው።
12ፀሐይም በገባች ጊዜ በአብራም ከባድ እንቅልፍ መጣበት፤ እነሆም፥ ድንጋጤና ታላቅ ጨለማ ወደቀበት፤
13አብራምንም አለው። ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ እወቅ፤ ባሪያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል።
14ደግሞም በባርነት በሚገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርዳለሁ፤ ከዚያም በኋላ በብዙ ከብት ይወጣሉ። q2 ኤሊዔዘር የተባለውን የግዕዙን መጽሐፍ ኢያውብር ይለዋል።
15አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ።
16በአራተኛው ትውልድ ግን ወደዚህ ይመለሳሉ፤ የአሞራውያን ኃጢአት ገና አልተፈጸመምና።
17ፀሐይም በገባች ጊዜ ታላቅ ጨለማ ሆነ፤ የምድጃ ጢስና የእሳት ነበልባል በዚያ በተከፈለው መካከል አለፈ።
18በዚያ ቀን እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን አደረገ። ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ትልቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ይህችን ምድር ለዘርህ ሰጥቼአለሁ፤
19ቄናውያንን ቄኔዛውያንንም
20ቀድሞናውያንንም ኬጢያውያንንም
21ፌርዛውያንንም ራፋይምንም አሞራውያንንም ከነዓናውያንንም ጌርጌሳውያንንም ኢያቡሳውያንንም።