ምዕራፍ 35
1እግዚአብሔርም ያዕቆብን አለው። ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ፥ በዚያም ኑር፤ ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጠልህ ለእግዚአብሔርም መሠውያውን አድርግ።
2ያዕቆብም ለቤተ ሰቡና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ እንዲህ አለ። እንግዶቹን አማልክት ከመካከላችሁ አስወግዱ፥ ንጹሐንም ሁኑ፥ ልብሳችሁንም ለውጡ፤
3ተነሥተንም ወደ ቤቴል እንውጣ፤ በዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ፥ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር መሠውያን አደርጋለሁ።
4በእጃቸው ያሉትንም እንግዶችን አማልክት ሁሉ በጆሮአቸውም ያሉትን ጕትቾች ለያዕቆብ ሰጡት፤ ያዕቆብም በሴኬም አጠገብ ካለችው የአድባር ዛፍ በታች ቀበራቸው።
5ተነሥተውም ሄዱ፤ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ሁሉ ወደቀ፥ የያዕቆብንም ልጆች ለማሳደድ አልተከተሉአቸውም።
6ያዕቆብም፥ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩት ሰዎች ሁሉ፥ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሎዛ መጡ፤ እርስዋም ቤቴል ናት።
7በዚያም መሰውያውን ሠራ፥ የዚያንም ቦታ ስም ኤልቤቴል ብሎ ጠራው፤ እርሱ ከወንድሙ ፊት በሸሸበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ተገልጦለት ነበርና።
8የርብቃ ሞግዚት ዲቦራም ሞተች፥ በቤቴልም ከአድባር ዛፍ በታች ተቀበረች፤ ስሙም አሎንባኩት ተብሎ ተጠራ።
9እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከሁለት ወንዞች መካከል ከሶርያ ከተመለሰ በኋላ እንደ ገና ተገለጠለት፥ ባረከውም።
10እግዚአብሔርም። ስምህ ያዕቆብ ነው፤ ከእንግዲህም ወዲህ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ፥ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ አለ፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው።
11እግዚአብሔርም አለው። ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፤ ብዛ፥ ተባዛም፤ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፥ ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ።
12ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለሁ።
13እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።
14ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ቦታ የድንጋይ ሐውልት ተከለ፤ የመጠጥ መሥዋዕትንም በእርሱ ላይ አፈሰሰ፥ ዘይትንም አፈሰሰበት።
15ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ያን ቦታ ቤቴል ብሎ ጠራው።
16ከቤቴልም ተነሡ፤ ወደ ኤፍራታም ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፥ በምጡም ተጨነቀች።
17ምጡም ባስጨነቃት ጊዜ አዋላጂቱ። አትፍሪ፥ ይኸኛው ደግሞ ወንድ ልጅ ይሆንሻልና አለቻት።
18እርስዋም ስትሞት ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ ስሙን ቤንኦኒ ብላ ጠራችው፤ አባቱ ግን ብንያም አለው።
19ራሔልም ሞተች፥ ወደ ኤፍራታ በምትወስድም መንገድ ተቀበረች፤ እርስዋም ቤተልሔም ናት።
20ያዕቆብም በመቃብርዋ ላይ ሐውልት አቆመ፤ እርሱም እስከ ዛሬ የራሔል የመቃብርዋ ሐውልት ነው።
21እስራኤልም ከዚያ ተነሣ፥ ድንኳኑንም ከጋዴር ግንብ በስተ ወዲያ ተከለ።
22እስራኤልም በዚያች አገር በተቀመጠ ጊዜ ሮቤል ሄደ የአባቱንም ቁባት ባላን ተገናኛት፤ እስራኤልም ሰማ። የያዕቆብም ልጆች አሥራ ሁለት ናቸው፤
23የልያ ልጆች፤ የያዕቆብ በኵር ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፤
24
25የራሔል ልጆች፤ ዮሴፍ፥ ብንያም፤ የራሔል ባርያ የባላ ልጆችም፤ ዳን፥ ንፍታሌም፤
26የልያ ባሪያ የዘለፋ ልጆችም፤ ጋድ፥ አሴር፤ እነዚህ በሁለቱ ወንዞች መካከል በሶርያ የተወለዱለት የያዕቆብ ልጆች ናቸው።
27ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ አብርሃምና ይስሐቅ እንግዶች ሆነው ወደ ተቀመጡባት ወደ መምሬ ወደ ቂርያትአርባቅ እርስዋም ኬብሮን ወደምትባለው መጣ።
28የይስሐቅም ዕድሜ መቶ ሰማንያ ዓመት ሆነ።
29ይስሐቅም ነፍሱን ሰጠ፥ ሞተም፤ ሸምግሎ ዕድሜንም ጠግቦ ወደ ወገኖቹ ተከማቸ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።