English

ምዕራፍ 43

1ራብም በምድር ጸና።
2ከግብፅም ያመጡትን እህል በልተው ከፈጸሙ በኋላ አባታቸው። እንደ ገና ሂዱ፤ ጥቂት እህል ሸምቱልን አላቸው።
3ይሁዳም እንዲህ አለው። ያ ሰው። ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልሆነ ፊቴን አታዩም ብሎ በብርቱ ቃል አስጠነቀቀን።
4ወንድማችንን ከእኛ ጋር ብትሰድደው እንወርዳለን፥ እህልም እንሸምትልሃለን፤
5ባትሰድደው ግን አንሄድም፤ ያ ሰው። ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልሆነ ፊቴን አታዩም ብሎናልና።
6እስራኤልም አላቸው። ለምን በደላችሁኝ? ለዚያውስ። ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለምን ነገራችሁት?
7እነርሱም አሉ። ያ ሰው ስለ እኛና ስለ ወገናችን ፈጽሞ ጠየቀን እንዲህም አለን። አባታችሁ ገና በሕይወት ነው? ወንድምስ አላችሁን? እኛም እንደዚሁ እንደ ጥያቄው መለስንለት፤ በውኑ። ወንድማችሁን አምጡ እንዲለን እናውቅ ነበርነን?
8ይሁዳም አባቱን እስራኤልን አለው። እኛና አንተ ልጆቻችንም ደግሞ እንድንድን እንዳንሞትም ብላቴናውን ከእኔ ጋር ስደደው፥ እኛም ተነሥተን እንሄዳለን።
9እኔ ስለ እርሱ እዋሳለሁ ከእጄ ትሻዋለህ፤ ወደ አንተ ባላመጣው፥ በፊትህም ባላቆመው፥ በዘመናት ሁሉ አንተን የበደልሁ ልሁን።
10ባንዘገይስ ኖሮ አሁን ሁለተኛ ጊዜ በተመለስን ነበር።
11እስራኤልም አባታቸው እንዲህ አላቸው። ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህንን አድርጉ፤ ከተመሰገነው ከምድሩ ፍሬ በዓይበታችሁ ይዛችሁ ሂዱ፥ ለዚያም ሰው እጅ መንሻ፥ ጥቂት በለሳን፥ ጥቂት ማር፥ ሽቱ፥ ከርቤ፥ ተምር፥ ለውዝ ውሰዱ።
12ብሩን በአጠፌታ አድርጋችሁ በእጃችሁ ውሰዱ፤ በዓይበታችሁ አፍ የተመለሰውንም ብር መልሳችሁ ውሰዱ፤ ምናልባት በስሕተት ይሆናል።
13ወንድማችሁንም ውሰዱ፥ ተነሥታችሁም ወደዚያ ሰው ተመለሱ።
14ሁሉን የሚችል አምላክም ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ከእናንተ ጋር ይሰድድ ዘንድ በዚያ ሰው ፊት ምሕረትን ይስጣችሁ፤ እኔም ልጆቼን እንዳጣሁ አጣሁ።
15ሰዎቹም በእጃቸው ያችን እጅ መንሻና አጠፌታውን ብር ብንያምንም ወሰዱ፤ ተነሥተውም ወደ ግብፅ ወረዱ፥ በዮሴፍም ፊት ቆሙ።
16ዮሴፍም ብንያምን ከእነርሱ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘው። እነዚያን ሰዎች ወደ ቤት አስገባቸው፥ እርድም እረድ አዘጋጅም፥ እነዚያ ሰዎች በእኩለ ቀን ከእኔ ጋር ይበላሉና።
17ያ ሰውም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ፤ ያ ሰውም ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባ።
18እነርሱም ወደ ዮሴፍ ቤት ስለ ገቡ ፈሩ፤ እንዲህም አሉ። በዓይበታችን ቀድሞ ስለ ተመለሰው ብር ሊተነኰልብን ሊወድቅብንም፥ እኛንም በባርነት ሊገዛ አህዮቻችንንም ሊወስድ ወደዚህ አስገባን።
19ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥም ቀረቡ፥ በቤቱም ደጅ ተናገሩት፥
20እንዲህም አሉት። ጌታዬ ሆይ፥ ቀድሞ እህልን ልንሸምት ወርደን ነበር፤
21ወደምናድርበትም ስፍራ በደረስን ጊዜ ዓይበታችንን ከፈትን፥ እነሆም፥ የእያንዳንዱ ሰው ብር በየዓይበቱ አፍ እንደ ሚዛኑ ብራችን ነበረ፤ አሁንም በእጃችን መለስነው።
22እህል እንሸምትበት ዘንድ ሌላም ብር በእጃችን አመጣን፤ ብራችንንም በዓይበታችን ማን እንደ ጨመረው አናውቅም።
23እርሱም አላቸው። ሰላም ለእናንተ ይሁን፥ አትፍሩ፤ አምላካችሁና የአባታችሁ አምላክ በዓይበታችሁ የተሰወረ ገንዘብ ሰጣችሁ፤ ብራችሁስ ደርሶኛል።
24ስምዖንንም አወጣላቸው። ሰውዮውም እነዚያን ስዎች ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባቸው፤ ውኃ አመጣላቸው፥ እግራቸውንም ታጠቡ፤ ለአህዮቻቸው አበቅ ሰጣቸው።
25ዮሴፍም በእኩለ ቀን እስኪገባ ድረስ እነርሱ እጅ መንሻቸውን አዘጋጁ፥ ከዚያ እንጀራን እንደሚበሉ ሰምተዋልና።
26ዮሴፍም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ በእጃቸው ያለውን እጅ መንሻ በቤት ውስጥ አቀረቡለት፥ ወደ ምድርም ወድቀው ሰገዱለት።
27እርሱም ደኅንነታቸውን ጠየቃቸው፥ እንዲህም አለ። የነገራችሁኝ ሽማግሌ አባታችሁ ደኅና ነውን? ገና በሕይወት አለን?
28እነርሱም አሉት። ባሪያህ አባታችን ደኅና ነው፤ ገና በሕይወት አለ። አጐንብሰውም ሰገዱለት።
29ዓይኑንም አንሥቶ የእናቱን ልጅ ብንያምን አየው፥ እርሱም አለ። የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነውን? እንዲህም አለው። ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ።
30ዮሴፍም ቸኮለ፥ አንጀቱ ወንድሙን ናፍቆታልና፤ ሊያለቅስም ወደደ፤ ወደ እልፍኙም ገብቶ ከዚያ አለቀሰ።
31ፊቱንም ታጥቦ ወጣ፥ ልቡንም አስታግሦ። እንጀራ አቅርቡ አለ።
32ለእርሱም ለብቻው አቀረቡ፥ ለእነርሱም ለብቻቸው፥ ከእርሱ ጋር ለሚበሉት ለግብፅ ሰዎችም ለብቻቸው፤ የግብፅ ሰዎች ከዕብራውያን ጋር መብላት አይሆንላቸውምና፥ ይህ ለግብፅ ሰዎች እንደ መርከስ ነውና።
33በፊቱም በኵሩ እንደ ታላቅነቱ ታናሹም እንደ ታናሽነቱ ተቀመጡ፤ ሰዎቹም እርስ በርሳቸው ተደነቁ።
34በፊቱም ካለው መብል ፈንታቸውን አቀረበላቸው፤ የብንያምም ፈንታ ከሁሉ አምስት እጅ የሚበልጥ ነበረ። እነርሱም ጠጡ ከእርሱም ጋር ደስ አላቸው።