ምዕራፍ 46
1እስራኤልም ለእርሱ ያለውን ሁሉ ይዞ ተነሣ፥ ወደ ቤርሳቤህ መጣ፥ መሥዋዕትንም ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ ሠዋ።
2እግዚአብሔርም በሌሊት ራእይ። ያዕቆብ ያዕቆብ ብሎ ለእስራኤል ተናገረው። እርሱም። እነሆኝ አለ።
3አለውም። የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ወደ ግብፅ መውረድ አትፍራ፥ በዚያ ትልቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና።
4እኔ ወደ ግብፅ አብሬህ እወርዳለሁ፥ ከዚያም ደግሞ እኔ አወጣሃለሁ፤ ዮሴፍም እጁን በዓይንህ ላይ ያኖራል።
5ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ተነሣ፤ የእስራኤልም ልጆች ያዕቆብን ይወስዱ ዘንድ ፈርዖን በሰደዳቸው ሰረገሎች አባታቸውን ያዕቆብንና ሕፃናቶቻቸውን ሴቶቻቸውንም ወሰዱ።
6እንስሶቻቸውንም በከነዓን አገርም ያገኙትን ከብታቸውን ሁሉ ይዘው ያዕቆብና ዘሩ ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ መጡ፤
7ወንዶች ልጆቹንና የልጆቹን ወንዶች ልጆች፥ ሴቶች ልጆቹንና የወንዶች ልጆቹን ሴቶች ልጆች፥ ዘሩንም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ አስገባቸው።
8ወደ ግብፅም የገቡት የእስራኤል ልጆች ስም ይህ ነው፥ ያዕቆብና ልጆቹ፤ የያዕቆብ በኵር ሮቤል።
9የሮቤልም ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ከርሚ።
10የስሞዖን ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ጾሐር፥ የከነዓናዊት ልጅ ሳኡል።
11የሌዊም ልጆች፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ።
12የይሁዳም ልጆች፤ ዔር፥ አውናን፥ ሴሎም፥ ፋሬስ፥ ዛራ፤ ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ፤ የፋሬስም ልጆች ኤስሮም፥ ሐሙል።
13የይሳኮርም ልጆች፤ ቶላ፥ ፉዋ፥ ዮብ፥ ሺምሮን።
14የዛብሎንም ልጆች፤ ሴሬድ፥ ኤሎን፥ ያሕልኤል።
15ልያ በመስጴጦምያ በሶርያ ለያዕቆብ የወለደቻቸው ልጆችና ሴቲቱ ልጅዋ ዲና እነዚህ ናቸው፤ ወንዶችም ሴቶችም ልጆችዋ ሁሉ ሠላሳ ሦስት ነፍስ ናቸው።
16የጋድም ልጆች ጽፎን፥ ሐጊ፥ ሹኒ፥ ኤስቦን፥ ዔሪ፥ አሮዲ፥ አርኤሊ።
17የአሴርም ልጆች፤ ዪምና፥ የሱዋ፥ የሱዊ፥ በሪዓ፥ እኅታቸው ሤራሕ፤ የበሪዓ ልጆችም፤ ሔቤር፥ መልኪኤል።
18ላባ ለልጁ ለልያ የሰጣት የዘለፋ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህን አሥራ ስድስቱንም ነፍስ ለያዕቆብ ወለደች።
19የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች ዮሴፍና ብንያም ናቸው።
20ለዮሴፍም በግብፅ ምድር ምናሴና ኤፍሬም ተወለዱለት፤ የሄልዮቱ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት የወለደቻቸው ናቸው።
21የብንያምም ልጆች፤ ቤላ፥ ቤኬር፥ አስቤል፤ የቤላ ልጆችም፤ ጌራ፥ ናዕማን፥ አኪ፥ ሮስ፥ ማንፌን፥ ሑፊም፤ ጌራም አርድን ወለደ።
22ለያዕቆብ የተወለዱለት የራሔልም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሁሉም አሥራ አራት ነፍስ ናቸው።
23የዳንም ልጆች፤ ሑሺም።
24የንፍታሌምም ልጆች፤ ያሕጽኤል፥ ጉኒ፥ ዬጽር፥ ሺሌም።
25ላባ ለልጁ ለራሔል የሰጣት የባላ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህንም ለያዕቆብ ወለደችለት፤ ሁሉም ሰባት ነፍስ ናቸው።
26ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት ሰዎች ሁሉ ከጉልበቱ የወጡት፥ ከልጆቹ ሚስቶች ሌላ፥ ሁላቸው ስድሳ ስድስት ናቸው።
27በግብፅ ምድር የተወለዱለት የዮሴፍም ልጆች ሁለት ናቸው፤ ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተ ሰዎች ሁሉ ሰባ ናቸው።
28ይሁዳንም በጌሤም እንዲቀበለው በፊቱ ወደ ዮሴፍ ላከ፤ ወደ ጌሤም ምድርም ደረሱ።
29ዮሴፍም ሰረገላውን አዘጋጀ፥ አባቱንም እስራኤልን ሊገናኘው ወደ ጌሤም ወጣ፤ ባየውም ጊዜ በአንገቱ ላይ ወደቀ፥ አቅፎትም ረጅም ጊዜ አለቀሰ።
30እስራኤልም ዮሴፍን። አንተ ገና በሕይወት ሳለህ ፊትህን አይቼአለሁና አሁን ልሙት አለው።
31ዮሴፍም ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው። እኔ መጥቼ ለፈርዖን እንዲህ ብዬ እነግረዋለሁ። በከነዓን ምድር የነበሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተ ሰዎች ወደ እኔ መጥተዋል፤
32እነርሱም በግ የሚጠብቁ ሰዎች ናቸው፥ እንስሳ ያረቡ ነበርና፤ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ያላቸውንም ሁሉ አመጡ።
33ፈርዖንም ቢጠራችሁ። ተግባራችሁስ ምንድር ነው? ቢላችሁ፥
34በግ ጠባቂ ሁሉ ለግብፅ ሰዎች ርኵስ ነውና በጌሤም እንድትቀመጡ እንዲህ በሉት። እኛ ባሪያዎችህ ከብላቴናነታችን ጀምረን እስከ አሁን ድረስ፥ እኛም አባቶቻችንም፥ እንስሳ አርቢዎች ነን። q ቍ@