English

ምዕራፍ 50

1ዮሴፍም በአባቱ ፊት ወደቀ፥ በእርሱም ላይ አለቀሰ፥ ሳመውም።
2ዮሴፍም ባለመድኃኒቶች አገልጋዮቹ አባቱን በሽቱ ያሹት ዘንድ አዘዘ፤ ባለመድኃኒቶችም እስራኤልን በሽቱ አሹት።
3አርባ ቀንም ፈጸሙለት፤ የሽቱ መደረጊያው ወራት እንደዚሁ ይፈጸማልና፤ የግብፅም ሰዎች ሰባ ቀን አለቀሱለት።
4የልቅሶውም ወራት ባለፈ ጊዜ ዮሴፍ ለፈርዖን ቤተ ሰቦች እንዲህ ብሎ ተናገረ። እኔ በፊታችሁ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩት።
5አባቴ አምሎኛል እንዲህ ሲል። እነሆ እኔ እሞታለሁ፤ በቈፈርሁት መቃብር በከነዓን ምድር ከዚያ ቅበረኝ። አሁንም ወጥቼ አባቴን ልቅበርና ልመለስ።
6ፈርዖንም። ውጣ፥ አባትህንም እንዳማለህ ቅበረው አለው።
7ዮሴፍም አባቱን ሊቀብር ወጣ፤ የፈርዖን ሎላልትም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወጡ፥ የቤቱ ሽማግሌዎችም የግብፅ ምድር ሽማግሌዎችም ሁሉ፤
8የዮሴፍም ቤተ ሰቦች ሁሉ ወንድሞቹም የአባቱም ቤተ ሰቦች ወጡ፤ ልጆቻቸውንና በጎቻቸውን ከብቶቻቸውን ብቻ በጌሤም ተዉ።
9ሰረገሎችም ፈረሰኞችም ከእርሱ ጋር ወጡ፥ ሠራዊቱም እጅግ ብዙ ነበረ።
10በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለችው ወደ አጣድ አውድማ መጡ፥ እጅግ ታላቅ በሆነ በጽኑ ልቅሶም አለቀሱለት፤ ለአባቱም ሰባት ቀን ልቅሶ አደረገለት።
11በዚያች ምድር የሚኖሩ የከነዓን ሰዎችም በአጣድ አውድማ የሆነውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ። ይህ ለግብፅ ሰዎች ታላቅ ልቅሶ ነው አሉ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ብለው ጠሩት፤ እርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ነው።
12ልጆቹም እንዳዘዛቸው እንደዚያው አደረጉለት፤
13ልጆቹም ወደ ከነዓን ምድር አጓዙት፥ ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻም ቀበሩት፤ እርስዋም በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት ዋሻ ናት።
14ዮሴፍና ወንድሞቹ አባቱንም ሊቀብሩ ከእርሱ ጋር የወጡት ሰዎች ሁሉ አባቱን ከቀበረ በኋላ ወደ ግብፅ ተመለሱ።
15የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እንዲህ አሉ። ምናልባት ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል፥ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል።
16ወደ ዮሴፍም መልእክት ላኩ እንዲህም አሉት። አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዞአል።
17ዮሴፍን እንዲህ በሉት። እባክህ የወንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል፥ እነርሱ በአንተ ከፍተውብሃልና፤ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉህን ይቅር በል።
18ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ በፊቱም ሰግደው። እነሆ እኛ ለአንተ ባሪያዎችህ ነን አሉት።
19ዮሴፍም አላቸው። አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን?
20እናንተ ክፉ ነገርን አሰባችሁብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው።
21አሁንም አትፍሩ፤ እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ። አጽናናቸውም ደስ አሰኛቸውም።
22ዮሴፍም በግብፅ ተቀመጠ፥ እርሱና የአባቱም ቤተ ሰብ፤ ዮሴፍም መቶ አሥር ዓመት ኖረ።
23ዮሴፍም የኤፍሬምን ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ አየ፤ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጆችም በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ።
24ዮሴፍም ወንድሞቹን አለ። እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም መጎብኘትን ይጎበኛችኋል፥ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል፤ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያደርሳችኋል።
25ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች። እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ አማላቸው።
26ዮሴፍም በመቶ አሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ፤ በሽቱም አሹት፥ በግብፅ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት።