ምዕራፍ 9
1እግዚአብሔርም ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው እንዲህም አላቸው። ብዙ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት።
2አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በምድር አራዊት፥ በሰማይም ወፎች፥ በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱትም፥ በባሕር ዓሦችም ሁሉ ላይ ይሁን፤ እነርሱም በእጃችሁ ተሰጥተዋል።
3ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ መብል ይሁናችሁ፤ ሁሉን እንደ ለመለመ ቡቃያ ሰጠኋችሁ።
4ነገር ግን ነፍሱ ደሙ ያለችበትን ሥጋ አትብሉ፤
5ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ፤ ከአራዊት ሁሉ እጅ እሻዋለሁ፤ ከሰውም እጅ፥ ከሰው ወንድም እጅ፥ የሰውን ነፍስ እሻለሁ።
6የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና።
7እናንተም ብዙ፥ ተባዙ፤ በምድር ላይ ተዋለዱ፥ እርቡባትም።
8እግዚአብሔርም ለኖኅና ለልጆቹ እንዲህ ብሎ ተናገረ።
9እኔም እነሆ ቃል ኪዳኔን ከእናንተና በኋላ ከሚመጣው ከዘራችሁ ጋር አቆማለሁ፤
10ከእናንተ ጋር ላሉትም ሕያው ነፍስ ላላቸው ሁሉ፥ ከእናንተ ጋር ከመርከብ ለወጡት ለወፎች፥ ለእንስሳትም ለምድር አራዊትም ሁሉ፥ ለማንኛውም ለምድር አራዊት ሁሉ ይሆናል።
11ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ አቆማለሁ፤ ሥጋ ያለውም ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም።
12እግዚአብሔርም አለ። በእኔና በእናንተ መካከል፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል፥ ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፤
13ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፥ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል።
14በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች፤
15በእኔና በእናንተ መካከል፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም።
16ቀስቲቱም በደመና ትሆናለች፤ በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘላለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ።
17እግዚአብሔርም ኖኅን። በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው አለው።
18ከመርከብ የወጡት የኖኅ ልጆችም እነዚህ ናቸው፥ ሴም፥ ካም፥ ያፌት፤ ካምም የከነዓን አባት ነው።
19የኖኅ ልጆች እነዚህ ሦስቱ ናቸው፤ ከእነርሱም ምድር ሁሉ ተሞላች።
20ኖኅም ገበሬ መሆን ጀመረ፥ ወይንም ተከለ።
21ከወይን ጠጁም ጠጣና ሰከረ፤ በድንኳኑም ውስጥ ዕራቁቱን ሆነ።
22የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው።
23ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም።
24ኖኅም ከወይን ጠጁ ስካር ነቃ፥ ታናሹ ልጁ ያደረገበትንም አወቀ።
25እንዲህም አለ። ከነዓን ርጉም ይሁን፤ ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን።
26እንዲህም አለ። የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፥ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።
27እግዚአብሔርም ያፌትን ያስፋ፥ በሴምም ድንኳን ይደር፤ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።
28ኖኅም ከጥፋት ውኃ በኋላ ሦስት መቶ አምሳ ዓመት ኖረ።
29ኖኅም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አምሳ ዓመት ሆነ፤ ሞተም።