ምዕራፍ 15
1አቤቱ፥ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?
2በቅንነት የሚሄድ፥ ጽድቅንም የሚያደርግ፥ በልቡም እውነትን የሚናገር።
3በአንደበቱ የማይሸነግል፥ በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ፥ ዘመዶቹንም የማይሰድብ።
4ኃጢአተኛ በፊቱ የተናቀ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን የሚያከብር፥ ለባልንጀራው የሚምል የማይከዳም።
5ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፥ በንጹሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል። እንዲህ የሚያደርግ ለዘላለም አይታወክም።