ምዕራፍ 16
1አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና ጠብቀኝ።
2እግዚአብሔርን። አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም።
3ፈቃድህ ሁሉ በምድር ባሉት ቅዱሳንና ክቡራን ላይ ነው።
4ወደ ሌላ ለሚፋጠኑት መከራቸው ይበዛል፤ የቍርባናቸውን ደም እኔ አላፈስሰውም፥ ስማቸውንም በከንፈሬ አልጠራም።
5እግዚአብሔር የርስቴ እድል ፈንታና ጽዋዬ ነው፥ ዕጣዬንም የምታጠና አንተ ነህ።
6ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ፥ ርስቴም ተዋበችልኝ።
7የመከረኝን እግዚአብሔርን እባርካለሁ፤ ደግሞም በሌሊት ኵላሊቶቼ ይገሥጹኛል።
8ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም።
9ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ምላሴም ሐሴት አደረገች፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤
10ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም።
11የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሐ አለ።